ይህን ጽሑፍ የሚያነብ ሰው የእርስበርስ ጦርነት የሚለውን አገላለጽ ለምን ተጠቀምክ ሊለኝ ይችላል፡፡ ስያሜው የሚያጣላን አይመስለኝም፡፡ በመፍረስ ላይ ባለች አገርም ሊሆን ይችላል፡፡ የፌደራል መንግሥትን ሥልጣን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ትንቅንቆች የፈጠሩት ሽብርም ሊባል ይችላል፡፡ ውስጣዊ ቅኝግዛትም ተባለ መንግሥታዊ ሽብር፣ ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚደረግ መውተርተርም ተባለ በስንት ስለት የተገኘ ሥልጣንን የማስጠበቅ የውልየለሽ አጥፊ አጀንዳዎች ትርዒት፣ የዘር ማጽዳትም ተባለ በዉጪ ኃይሎች የሚዘወር አለመረጋጋት ለማናቸውም ስያሜውን ለጊዜው ለባለሙያዎች እንተውላቸው፡፡
እዚህ ደረጃ ላይ ለምን ደረስን የሚለውን ሁላችንም በልምድና ዕውቀታችን ልክ ለመመለስ እንሞክር፡፡ እዚህ እሳት ውስጥ ራሳችንን ላለማግኘት ለምን አልሞከርንም የሚለውንስ አስበንበት ይሆን? ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም እንዲሉ አሁን በዚህ ሁኔታ ላይ መውደቃችንን እንጂ ስላለፈው ብዙ መጨነቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ሞቶ፣ ሌሎች ሚሊዮኖች የአገር ውስጥ ስደተኞች ሆነው፣ ከቁጥጥር ዉጪ ሊወጣ የሚታገል የኢኮኖሚ ችግር ነግሦ፣ በየቦታው ሥርዓት አልበኝነት ሰፍኖ፣ ረሃብ ፀንቶ፣ የአጋች ታጋች ድራማዎች በዝተው፣ ኢትዮጵያ የማትመስል አገር ውስጥ እየኖርን፣ ስለነገ ፈጽሞ እርግጠኛነት አጥተን እያልን መቀጠል እንችላለን፡፡ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት አስጊ ሁኔታዎች ብዙዎቹን እያስተናገደች ባለች አገር ውስጥ እንዴት እንኑር? እስካሁንስ ያለፉትን አምስት ዓመታት እንዴት ኖርን? እነሆ አንዳንድ ነጥቦች፡፡
ሰዎች በተለያዩ ነገሮች ተጠምደዋል፡፡ ነጋዴዎች ሆነው በየዕለቱ በሚንረው የዋጋ ግሽበት ምክንያት ብራቸው ሚሊዮን ገብቶ ሲራባ ልባቸው ጠፍቶ ሌሎች ሚሊዮኖችን ፍለጋ ይቃትታሉ፡፡ ወይም ሁለት ከተሞች ላይ የሚሰሩ ተቀጣሪዎች ሆነው ከአንዱ ወደ ሌላው ከተማ እየተመላለሱ ይኖራሉ፡፡ ባሉበት እንደምንም ሊያሟሉት የሚችሉትን አገልግሎት ለማግኘት ወደ ትልቅ ከተማ ይሄዳሉ፡፡ በአጭሩ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እስከ ዛሬ በብዙ ሰዎች ዘንድ ያየሁት ክፍተት ቢኖር መጓጓዛቸውን እንጂ የሚጓጓዙበት መንገድ ወይም መዳረሻቸው ሰላም መሆኑን እንደማይከታተሉ ነው፡፡ በእርግጥ ሰላም ባይሆን ሾፌሩ ይነግረን ነበር፣ መንገድ ይዘጋ ነበር፣ እንሰማ ነበር ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ በአጋጣሚ ስለ መንገዱና መዳረሻቸው ከሌላ አካል መረጃ ልንሰማ እንችል ይሆናል ከማለት ሌሎችን የማወቂያ መንገዶች ሆነ ብሎ ማጥናትና መፈለግ ግድ ይላል፡፡ ሾፌሩ ያልነገራችሁ እሱ ወደሚሄድበት አቅጣጫ ከሱ ብሄር፣ ከመኪናው ታርጋ፣ ካለው ትውውቅ፣ ከኃይማኖቱ ወይም ከሚናገረው ቋንቋ አንጻር በግሉ ችግር አይገጥመው ሆኖስ ቢሆን? መንገዱ ያልተዘጋው ያን ያህል ለትራፊክ አሳሰቢ ነገር የለም ብለው በወሰኑ የመንገድ ትራንስፖት ሰዎች ወይም አገሩ ሰላም ነው የሚል ስዕል ለመሳል በፈለጉ ፖለቲከኞች ውሳኔ ቢሆንስ? አንዳንዴ መሄድ ችግር የለው ይሆናል፡፡ መምጣት ከባድ ይሆናል፡፡ ለአንዱ ችግር የሌለው ለሌላው ይኖረዋል፡፡ ሚሊዮኖች በሚሞቱበት አገር መቶ ሰዎች ሊሞቱ ወይም የተወሰኑ ሺዎች ሊንገላቱ ይችላሉ ብሎ የሚጠነቀቅላችሁ ያለ ይመስላችኋል? እንዳትታለሉ! እንሰማ ነበር የሚለውም አይሰራም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አይገመቴ ሁኔታዎች የመፈጠር ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ሾፌሩም አይነግራችሁም፣ መንገዱም አይዘጋም፣ ልትሰሙ የምትችሉበትም ዕድል የለም፡፡ ‹‹ታዲያ ምን ተሻለን?›› ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ገና ለገና ችግር ሊመጣ ይችላል ብሎ አስጨነቀን ብላችሁኝም ይሆናል፡፡ ግድ የላችሁም፡፡ ትንሽ ሃሳብ እናፍልቅ፤ ካለፉትም ጊዜያት እንማር፡፡ የሚፈጠሩት ችግሮች በአመዛኙ በፖለቲካ ውሳኔ የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ አንድ ቡድን ወይም አካል አንድን ግብ ለመምታት ሲል የሚያደርጋቸው ናቸው፡፡ እንጂ ተራ የእንትን ብሔር ወይም ኃይማኖት አባል ተበድዬ፣ ምን ብዬ ብሎ አይነሳም፤ አይነካችሁምም፡፡ ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚወስዷቸው እርምጃዎች በጣም ውሱን ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቡድኖች የሚያንቀሳቅሷቸውን ርዕሰጉዳዮች መከታተልና የአካሄዳቸውን አዝማሚያ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ መረጃዎቹ ከየት ይገኛሉ ከተባለ ከመደበኛ ሚዲያዎች፣ ከማህበራዊ ሚዲያዎችና ከሌሎች ምንጮች ይሆናል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካ አካሄድ በንቃት መከታተል ሕይወትን የሚታደግ ውሳኔ ላይ ሊያደርስዎት ይችላል፡፡ ፖለቲካውን እንኳን ባይከታተሉ መደበኛ ዜና ይከታተሉ፡፡ መደበኛ ሚዲያዎች ጭራሽ የማይዘግቧቸው ወይም ዘግይተው ምናልባትም አዛብተው የሚዘግቧቸው መረጃዎች አሉ፡፡ ቴሌቪዥን አይቼ፣ ሬዲዮ ሰምቼ፣ የእንትን ሚዲያን አካውንት ሰብስክራይብ አድርጌ ዩቱብ ላይ ሰምቼ አይሰራም፡፡ መደበኛ ሚዲያዎች መረጃዎቹን አጣርተው፣ አለቆቻቸውን አስፈቅደው፣ ግራ ቀኙን አይተው፣ ወሬውን እስኪለቁት ብዙ ውድመቶች የመጡባቸውን ጊዜያት አስቡ፡፡ መረጃ እንዲዳፈንም ይደረጋል፡፡ መረጃ ተዛብቶ ይደርሳችኋል፡፡ ወይም ይዘገያል፡፡ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ስንመጣ ታማኝ የሚሏቸውን ዘጋቢዎች ይለዩ፡፡ እነርሱም ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ አውቀው የሆነ ዓላማ ለማሳካት፣ ብዙ ተከታይ ለማግኘት፣ ሰበር ዜና ለማውጣት ወይም የመረጃ ምንጭ አሳስቷቸው፣ ምናልባትም ከሁለት ወገን ሳያጣሩ ዘግበው ሊሆን ይችላል፡፡ መረጃዎችን ማን ለቀቃቸው የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ ያንን መረጃ ከየት አመጣው የሚለውም እንዲሁ፡፡ ግነትም ካለ ልብ ይበሉ፡፡ ስለዚህ የማህበራዊ ሚዲያን መረጃ በሚገባ ማጣራት ያሻል፡፡ በፌስቡክ ገጽዎ የመጡልዎትን ወይም እርስዎ ላይክ ካደረጓቸው ገጾችና አካውንቶች ገብተው ያዩትን ብቻ አይጠቀሙ፡፡ ፈልግ የሚለውን ተጠቅመው ይፈልጉ፡፡ ፍለጋዎትን መረጃው በተለቀቀበት ጊዜ፣ ቦታ፣ ምንጭ መሰረት ማጥራት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ከሆነ በከተሞቹ ስም፣ በብሔሮች፣ በፓርቲዎች፣ በኃይማኖቶች ወዘተ የዕለቱን መረጃ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ የፌስቡኩ ለትዊተርም፣ ከቲክቶክም ይሰራል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያን በዚህ መልኩ ከተጠቀሙ ወደሚያውቋቸው ሰዎች መረጃ ፍለጋ መደወል ሊኖርብዎት ይችላል፡፡ ከሚዲያ ሚዲያ፣ ከአካውንት አካውንት፣ ከግለሰብ ግለሰብ የወሰዱትን መረጃ ማማሳከርና በውሳኔ ግብዓትነት መጠቀም እንጂ ሌሎች ሰላም ነው ብለው በወሰኑት ውሳኔ ተመስርተው ሕይወትዎንና የሚወዷቸውን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ አይጣሉ፡፡ ዘዴ ይፈልጉ፡፡ የመስሪያ ቤት መታወቂያ ያሳያሉ ወይስ የቀበሌ፣ በግልዎ መኪና ይሄዳሉ በህዝብ ትራንስፖርት፣ በሚኒባስ ወይስ በአውቶቡስ፣ ቢጠየቁ ሙያዎትንና ስራዎትን ይደብቃሉ ወይስ ግልጹን ይናገራሉ? መታወቂያው ላይ ስሙ የፊደል ግድፈት እንዳለው ላስቆሙት አካላት በመንገር ራሱን የሌላ ኃይማኖት አባል በማስመሰል ሸወዶ እንዳለፈው ወዳጄ ሕይወትዎን ያተርፋሉ? ከመንገዱ በኋላስ? የሚያርፉበት ከተማ ሰላም ነው? እስከመቼ? ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ እንወያይበት፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ