የሳሲት ወጎች
ቁጥር 5
የቅዳሜ ገበያተኞች ድብድቦችና ትዝታዎቼ
ስለ እውነት ለመናገር በፊት በፊት ሰዎች ስለ ሳሲት መልካም ሊባል የማይችል ዕይታ ነበራቸው። ይኸውም ከሌላ ችግር የመነጨ ሳይሆን ከፀብ፣ ከግጭትና ከግድያ ጋር የተያያዘ ነው። አስደንጋጩ የሳሲት ገጽታ በአገሬው መካከል እንጂ እንግዶችን ስለማይነካካ አይደናገጡ። በሃያ ዓመታት ልዩነት የተከሰቱ ተመሳሳይ ነገሮችን እንመልከት። አንደኛው ጋሽ ዳምጠው ደጅ በደርግ ጊዜ፣ ሌላኛው ጋሽ ደመቀ ደጅ በ1990ዎቹ የተከሰቱ ናቸው። ጉዳዩ እንዲህ ነው። ፀብ ይነሣል - ያውም ተመጣጣኝ ባልሆኑ ወገኖች መካከል። አንደኛው ወገን ዱላ ይዟል፤ ሌላኛው ጠመንጃ። የትኛው እንደሚያሸንፍ ግልጽ ነው። መሸናነፍ ብቻ ሳይሆን ሟችና ገዳይ መሆን ይከተላል። በሁለቱም የግጭቱ መንስኤ የዱላዎቹ ትዕግስት ማጣት እንደሆነ ሰምቻለሁ። ባለ ዱላ ከባለ ዱላ፣ ባለ ጠመንጃ ከባለ ጠመንጃ የሚጋጠሙበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ስካር ጠባቸውን ሊያባብስ ወይም መንስኤ ሊሆን ይችላል። የጠባቸው ስር መሰረት ከመሬት ወይም ከሴት አይርቅም። በሀብት ሊቀናኑ ወይም በወሬ ሊጣሉም ይችላሉ። ፖሊስ ወይም ተረኛ ታጣቂ ህግ ማስከበሩ አይቀርም። ይሁን እንጂ በብዛት ፖሊሶች ጥይት ሲሰማ ወይም ጠብ አለ ሲባል አይገኙም። ነገሩ ካለቀ በኋላ ተፈልገው ይመጣሉ። የፖሊስ ጭካኔም ከፍ ያለ ነው። በዱላ ሲደበድቡ ርህራሄ የሚባል የፈጠረባቸው አይመስሉም። ሐኪም ቤትም ዘወትር ቅዳሜ ስራ ይበዛበታል። የተፈነከተን መስፋትና ደም ማስቆም መደበኛ ስራቸው ይመስላል። ብዙ ሐኪሞች በብዙዎች ልብ ውስጥ አሉ። ይህን ሁሉ የመጨረሻ ትዕይንት አስቀደምኩ እንጂ ቅዳሜ ጠዋት ገበያተኛው ከየአጎራባች የገጠር መንደሮችና አካባቢዎች ሲመጣ ያለውን ዉበት አልዘነጋሁም። የእህል ምርታቸውን ተሸክመው፣ አዝለው ወይም በአህያ ጭነው በተቻላቸው መጠን ተውበው ከሩቅ በብዛት ሲመጡ ይስባሉ። ወንዶቹም ሴቶቹም ረጅሙን መንገድ ጨርሰው ሳሲት ሲደርሱ ወደየዘመዶቻቸውና ደንበኞቻቸው ቤት ጎራ ብለው ሰላምታ ያቀርባሉ፤ ዉኃ ጥማቸውንም በዉኃ፣ ጠላ ወይም ለስላሳ ይቆርጣሉ። ወግና ጥየቃው ይቀልጣል። በቀጥታ ወደ ገበያ ሄዶ ሸመታውን የሚያከናውንም አለ። የዕለቱ ጉዳይ ከተተኮሰ በኋላ የመጠጡም ሆነ የምግቡ ገበያ ይቀልጣል። ጠላው፣ አረቄው፣ ጠጁ፣ ቢራው ወዘተ ይንቆረቆራል። ጠቡ በስካር ምክንያት የሚመጣ መሆኑን ከዚህ መገመት ይቻላል። ሌሎችም ምክንያቶች አይጠፉም። የቅዳሜ ገበያ ትርዒት (የጋማ ከብቱንና ጥቂት መኪኖችን ጨምሮ) ሳሲትን ከሚያደምቋት ዋነኛው ነው።
ቁጥር 6
የሳሲት ማስተር ፕላን ... ይቀጥላል