ዓርብ 30 ጁን 2023

የሳሲት ወጎች ቁ. 3 አራጅ የመጣ ቀን

 የሳሲት ወጎች ቁ. 3

አራጅ የመጣ ቀን


ሳሲት ስናድግ እንደዛሬ ልጅ ጫማ የለንም። በክረምት ወቅትና እስከ ጥር በግ እናግዳለን። ከመስከረም እስከ ጥር ግማሽ ቀን በግ አግደን ግማሽ ቀን እንማራለን። ጉልበታችንን ለሚፈልጉት ቤተሰቦቻችን ትምህርት በፈረቃ መሆኑ ተወዷል። ነገሩ የመማሪያ ክፍል እጥረትን ለመፍታት የተዘየደ መላ ሊሆን ቢችልም። ስናድግ አስፈሪ ነገሮች አዘውትረው ይወራሉ። የሰዎች በተለያዩ መንገዶች መጎዳትና መሞት የሚታወቅ ቢሆንም አንዳንድ ትረካዎች በተለይ ተጨማሪ ጫና ይፈጥሩብናል። የጭራቅ ነገር ያስፈራናል። "ዱሮ አያቶቼ ቤት መጥቶ ነበር አሉ። አራት ዓይኖች አሉት። ከኋላ ያሉትን ሁለት ዓይኖች በሻሽ ሸፍኗቸዋል። እንጀራ እንዲሰጡት ጠይቆ ሁለት እንጀራ ሲሰጡት በአንዴ ጎረሰው። ዉኃ በአቦሬ ጨምረውለት በአንዴ ጨለጣት።" ትላለች ዓለምሸት ሞሰብ እየሰፋች። እኔ ፍርሐት ይዞኛል። ይህ ትረካ የበለጠ የሚያስፈራኝ ከሰው ጋር ስሆን ሳይሆን በጨለማና ዱር ወይም ጫካ በጎች ሳግድ ነበር። በጨለማ ብፈረም መብራት በማብራት ፍርሐቴን እቀንሳለሁ። የዱሩም ትልቅ ሰው ወዳለበት በመሮጥ ለማምለጥ አስባለሁ። አንድ ቀን አይጥ ዉኃ ጋ በጎች ሳግድ አህዮች የሚነዱና አለባበሳቸው ጭራቅ የሚመስሉ ሰዎች አየሁ። ጭራቅ ባይሆኑ እንኳን አራጅ ይሆናሉ ብዬ ገመትኩ። አራጅ የሰው ደም የሚሸጥ ነው ይባላል። ወፍጮና መኪና በሱ ነው የሚሰራው ተብሎ ይታመናል። "ያለዚያማ ይህን ሁሉ እህል እንዴት ይፈጨዋል! የአጋንንት ሥራ ነው።" ይሏችኋል። አራጅም ሆኑ ጭራቅ ሰው ወዳለበት መሄድ አማራጬ ሆነና እየራቅሁ ሄድኩ። ቢያንስ አበባ የግሌ ጓሮ ባለው ጫካ አንድ ሰው ተሸፍኖ እየጮኸ እንዳስፈራራኝ ዕለት እየጮህኩ አልሮጥኩም። ገሸሽ ብዬ አሳለፍኳቸው። ምንም አልተተናኮሉኝም። በኋላ ማታ ወደ ቤት ስመጣ በሰፈራችን ባለ ቤት ደጅ አህዮቻቸው ታስረዋል። ሰዎቹም ጠላ ይጠጣሉ። ለካ ጭራቆች አይደሉም። ላሊበላዎች ናቸው አሉ። አይ ልጅነት! 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...