2023 ጁን 29, ሐሙስ

የሳሲት ወጎች ቁ. 2 ሙስሊም የመጣ ቀን

የሳሲት ወጎች

ቁ. 2

ሙስሊም የመጣ ቀን


እስኪ አስቡት። ወረዳው ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሊሆን ትንሽ የቀረው ነው። ያለው መስጊድ ከአንድ አይበልጥም። ያውም የወረዳችን ጫፍ ስገሮ ቆላ። በእውነት የስገሮ ቆላን ሙስሊሞች ወግ ቅዳሜ ገበያ የሚመጡ ዘመዶቼ ሲያወሩ ነበር የሰማሁት። የአሁኑን ትውልድ ብትጠይቁት "ቀጣፊ" ሊላችሁ ይችላል። "እኛ ወረዳማ ተክርስቲያን ዉጪ የለም" እንደሚሏችሁ አትጠራጠሩ። እነዚያ ሙስሊሞች ወደ ክርስትና ተቀይረዋል ወይም እየተቀየሩ ነው የሚል ወሬ ሰምቻለሁ። ይህ ታዲያ የዛሬ 25 ዓመት የነበረ ወሬ ነው። እስልምና እንኳን አረብ አገርንና አፍሪካን አውሮፓንና አሜሪካን በአስገራሚ ፍጥነት እያዳረሰ ስላለ መሐመድም ሆነ ሠይድ የተጉለት እስልምና መጥፋት ግድ አይላቸውም። ያው በጥናትና ምርምር ሰበብ ልክ አይሁዶች ብረትና ሸክላ ሰሪ ሁሉ የኛ ነው ብለው ሰሜን ሸዋ ገብተው ውስጥ ውስጡን ወታደርና ዘመናዊ ባሪያ ምልመላውን እንደተያዙት ሁሉ አረቦችም ሊመጡላችሁ ይችላሉ። ግፋ ቢል ሙስሊም እንጂ አረብ ነኝ የሚል አማራ አይኖርም መቼም። የአረብ ቤት ባለቤት ክልስ አረቦችን አይጨምርም። ምን አለፋችሁ፣ ሳሲት ሙስሊም አይታወቅም ነበር። 1988፣ 89፣ 90 ሂዱ። በእርግጥ እንደ አሁኑ ጳድቃኔ ማርያም ታዋቂ ገዳም ሳትሆን እኛ ጋ ከሩቅ ሰዎች የሚመጡት ወፋ ነገሠን ፍለጋ ነበር። ታዋቂው ከበርቴ ባለውቃቢ የአገሩ መመኪያ ነበሩ። መኪናውም ሆነ ንግዱ በእርሳቸው ሰበብ የመጣ ነበር። እርሳቸው ጋ የሙስሊም መቃብር አለ ሲባል ሰምቻለሁ። ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያን እርሳቸው ጋር ይሄዳሉ። አያቶቼ ቤት በጃንሆይ ጊዜ ሦስት ወፋ ጋ ለመሄድ የመሸባቸው ሙስሊሞች አድረው ነበር አሉ። ስለ አሰጋገዳቸው፣ ስለ ቡና ስጦታቸው፣ ስለ ምርቃታቸው መድረስ (የልጅ ጎረቤት ይስጣችሁ)  አሁንም በፍቅር ይወራል። ስለዚህ አጋጣሚ በትዝታ ይነሳል እንጂ የእስላምና ክርስቲያን ድንበር በትክክል የተሰመረ ነው። በዚህም ሰበብ ሙስሊም እፈራ ነበር። መቼም ኢዝላሞፎቢክ የሚለኝ አይኖርም። ቢኖርም ጥረቱ በቀጣዮቹ መስመሮች ፉርሽ ይሆንበታል። ወደ ወፋ የሚወርዱ ሴቶች ሙስሊሞች "ወላሂ" ሲሉ ሰምቻለሁ። ወፋም ክርስቲያንና ሙስሊሙን ሌሊት በየተራ ሲያስተናግዱ "አማሮች ደህና እደሩ፤ የተጨነቀች የእስላም ነፍስ ትጠበቀኛለች" ይላሉ። የሳሲቱ ሙስሊም ከመምጣቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት አንድ አርበኛ እኛ ደጅ የምሽት ፀሐይ ሊሞቁ መጥተው ከሽማግሌዎች ጋር ሲያወሩ ያሉትን አስታውሰዋለሁ።

"አብዬ፣ እዚያ ደብረብርሃን የስላሙን መስጊድ አይተኸዋል?" 

"አዋድ"

"ለምንድነው እንደዚያ የረዘመው!" 

"እንዲቀርበው ነዋ ላላህ።"

"አላሁኣ ክበር የሚለውስ?" 

"እንዲበለጥግለት መሰለኝ።"

ሁለቱ ኃይማኖቶች ተከባብረዋል፤ ተዋግተዋል፤ ተቀላልደዋል። ይህም አይደንቀኝም። 

መሐመድ የመጣው አዲስ በተከፈተው ዳቦ ቤት ለመጋገር ነበር። ወጣቶችና ልጆች የመሐመድን ዳቦ በልተዋል። እኔ መሐመድ በተቀመጠበት ወንበር መቀመጥ እፈራ ነበር። ሽማግሌዎች ግን ስሙን መጥራት እንኳን ከብዷቸው ማሞ ብለው ጠሩት። ማናቸውም ወጣት ሊጠራ በሚችልበት። ባይተዋርነቱ ያልተመቸው መሐመድ የባለ ዳቦ ቤቱ ልጅ ክርስትና ስትነሣ ነተሣ። ክርስትና ስምም ወጣለት። አረብ አገር ሲሄዱ እንደሚሰልሙት። ቀጥሎ ሐኪም መሐመድ መጣ። ሰዎች በእርሱ መሮፌ ለመወጋት ማቅማማታቸውን ሰምቻለሁ። በኋላ ደግሞ ሌላ ጫት ቃሚ መምህር መሐመድ መጣ። ሳሲቶች ሙስሊም ሲያገኙ መሐመድ ብለው የሚጠሩበት ምክንያት ገባችሁ? ሴት ሙስሊም ማን ትባላለች ያለኝም አለ። ከዚያ ወጥቼ በርካታ ሙስሊም ጓደኞች ያሉኝ ሰው ነኝ።

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...