ሐሙስ 29 ጁን 2023

የሳሲት ወጎች ቁ. 1 ጴንጤ የመጣ ቀን


ሳሲትን በበርካታ ጽሑፎቼ ነካክቻታለሁ። አንዳንዶች ለድርሰት ማሳመሪያ በምናቤ የፈጠርኳት ቀዬ ትመስላቸዋለች። እኔ ግን እላለሁ - በእውን ያለች ገጠር ቀመስ ከተማ ነች። በፊት እንደጻፍኩላችሁ እኛ ስናድግ በሳሲት መሬት የሌለው ወይም የማያርስ ሰው አልነበረም ለማለት እደፍራለሁ - ከጥቂት የመንግስት ሰራተኞችና ከአንዳንድ ምስኪን ነዋሪዎች በስተቀር። ለመጨረሻ ጊዜ ትቻት የሄድኩት በ1992 ዓ.ም. ነበር። ይሁን እንጂ ማንነቴን ለመቅረጽ የሚያስችላትን መሰረታዊ ዕድሜ ኖሬባታለሁ። የሳሲት ወሬ ሳይደርሰኝ የቀረበት ሳምንት እምብዛም የለም። በሳምንት ባይሆን በሁለት ሳምንት ከዘመድ ወዳጅ ወይም ከእንግዳ እሰማለሁ። በለቀቅሁበት ዓመት የሰማሁት የጴንጤዎች ወደ ሳሲት መምጣት ትልቅ ወሬ ነበር። በመኪና መጡ። የበፊቱ ገበያ ላይ ጄኔሬተር አስነሱ። ፊልም ከፍተው ማሳየት፣ በየመሐሉም ማስተማር ጀማመሩ። ትምህርቱ መንፈሳዊ ቢሆንም የተለመደው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ባለመሆኑ የተበሳጩ ሰዎች እምነታችንን ሊያስክዱን ነው ብለው የድንጋይ ናዳ አወረዱ። ሽብር ተፈጠረ። ፖሊስ ጣልቃ ገብቶ የጴንጤዎቹን ሕይወት ታደገ። ያለ ምንም ጉዳት አመለጡ። በእርግጥ አስቀድሞም እየዞሩ አንዲት ትንሽ ሰማያዊ እርጉዝ መጽሐፍ ሲያድሉ ተይዘዋል አሉ። ከአዲስ አበባ የመጡ የሳሲት ተወላጆች ናቸው። ሌላ ጊዜ ባደረኩት ማጣራት በዚህ ሁኔታ የተቆጣ ካህን አልነበረም። ፖሊስ የሰዎችን ጥቆማ መሰረት አድርጎ ጴንጤዎቹን አስሮ ካህናትን በምስክርነት ጠርቶ ነበር አሉ። ካህናቱ መጽሐፉ ላይ ያለው የእግዚአብሔር ቃል ነው ነበር ያሉት። ምናልባት ቆይቼም የጠየኳቸው ካህናት በመጽሐፏ ላይ "ዶጮ መስቀል" ከመታተሙ በቀር የእግዚአብሔር ቃል ታትሟል ብለዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ፈጽሞ ፍላጎት ስለሌለኝ በድጋፍም በተቃውሞም ሐሳብ መስጠት አልችልም። ተራኪ ነኝ። ሳሲት ጴንጤ የሚባል ነገር ያወቅሁት አንድ አስተማሪያችን ጴንጤ መሆናቸውን በመስማቴ ነበር። በእርግጥ አንደኛና ሁለተኛ ክፍል አስተምረውን የሄዱ ሌላ ጴንጤ መምህርም ነበሩን። እኔን በተለይ ያቀርቡኛል። ይቀልዱልኛል። "መዘምር፣ እስኪ ሚስት ፈልግልኝ" ይሉኛል። እስቃለሁ። "ጡቷ አጎጠጎጤ የሆነ፣ ተረከዟ ... ፀጉሯ ... " እስቃለሁ። ሳሲትን አልፎም ገጠር ውስጥ ጴንጤ መምህር ነበሩ። ስምንተኛ ክፍል ሆነን ጴንጤ ሐኪም መጣች። የጥምቀት ዕለት ሁሉም ሰው ጥምቀት ሲሄድ ብቻዋን ቀረች። ስላሳዘነቻት የአጣዬዋ ተወላጅ ዘመዳችን ዓለምነሽ አብራት ቆየች። የጴንጤዎች ድፍረት ሲገርመኝ ይኖራል። ሁሉንም ሰው ጴንጤ ለማድረግ ይጣጣራሉ። 

ቀጣይ - ሙስሊም የመጣ ቀን

 

ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...