የሳሲት ወጎች
ቁ. 13
ሳሲቶች በምን ይዝናናሉ?
ገጠርን ስታስቡ ምን ይሰማችኋል? የመዝናናት ስሜት ይመጣባችኋል? ወይስ ይጨንቃችኋል? እስኪ በሁለት በኩል ሊነሱ የሚችሉ ሃሳቦችን እናንሳ፡፡
ገጠር እንደሚያስደስታቸው፣ እንደሚያዝናናቸውና ሰላም እንደሚሰጣቸው የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ ገጠር ከሁካታ የራቀ ሰላማዊ ቦታ ተደርጎ ይታያል፡፡ የአየሩ ንጽህና፣ የሰዉ የዋህነት፣ የህይወቱ ቀላልነት፣ የምግቡ ተፈጥሯዊነት ተደማምሮ ገጠርን የመሰለ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ቢል የለባችሁም፤ የቤት ኪራይ ደረሰ አትሉም፡፡ ነዳጅ አያሳስባችሁም፡፡ ምን ብዬ ልንገራችሁ? በተለይ በከተሜ ዓይን ሳየው ይህንን አያለሁ፡፡ ከዚህኛው የወንዙ በኩል ሆኖ ሲያዩት የዚያኛው በኩል የበለጠ ይጣፍጥ ይመስላል እንዲሉ ላሞች፡፡
ገጠር የሚያንገሸግሸው አለ፡፡ አንድ አጎቴ አለ፡፡ አደናውሰኝ ዘነበ ይባላል፡፡ አረም የሚያርምበትም ሆነ እርሻ የሚያርስበት ማሳው ዋሻ በተባለ ቦታ ይገኛል፡፡ ጠዋት የወጣ በዚያ በተራሮች በተከበበ ቦታ በሚገኘው ማሳው ላይ ሲሰራ ውሎ ማታ ሲመለስ ነው ሰው የሚባል የሚያየው፡፡ በጣም ይጨንቀኛል ይላል፡፡ ሌላ ቀን እናቴ ለምናው ከሳሲት ወደ ሰላድንጋይ ከሚወስደውና ወስዶ ከሚመልሰው መኪና መንገድ ዳር ባለው መሬቷ ላይ ሲያርሙ ይውላሉ፡፡ ከሰው ጋር እያወሩ ማረም የበለጠ እንደሚያስደስተው ነገራቸው፡፡ መንገድ ዳር በሚገኘው ማሳ ላይ በመዋሉም መንገደኞችንና መኪኖችን እያየ ይዝናናል፡፡ ከዚህች ንጽጽር እንኳን ስናይ ገጠር የሚያስጨንቀውና ከተማና የሥልጣኔ ትሩፋት የሚያስደስተው አለ፡፡
ገጠር የሚያስደስታቸው ለአንድና ሁለት ቀን የሆነም አይጠፉም፡፡ ዘመድ ለመጠየቅ፣ ለለቅሶ፣ ለሰርግ፣ ለንግሥ፣ ለመንፈሳዊ ጉዞ ወዘተ ብቅ ብለው የሚመጡ አሉ፡፡ ‹‹ክረሙ›› ብተሏቸው ‹‹ግደሉኝ›› ብለው ይቃወማሉ፡፡ ‹‹ልጄ፣ ሜስቴ፣ ዕቁቤ፣ ፓርቲዬ ብለው ልሂድ ይላሉ፡፡
ገጠር የሚያንገሸግሻቸው በአንዳንድ ሁኔታ እንጂ ከገጠር ስብዕና አይወጡም፡፡ የከተማ ሁካታ ሲሰማቸው መልሰው ያቺው ገጠሬ ይላሉ፡፡ ከላይ ያየነው አደናውሰኝ ስለ ሥልጣኔ ለማየት የቻለው ዘግይቶ ነው፡፡ የቄስ እንጂ የመንግስት ትምህርት አልተማረም፡፡ ሰላድንጋይን እንኳን በ30 ዓመቱ አየ፡፡ አዲስ አበባን ቢያይ መንግስተሰማያት ሊመስለው ይችላል፡፡ ቆይቶ ሲኦል ነው ሊልም ይችላል፡፡ ያብለጨለጨ ሁሉ ወርቅ አይደለምና፡፡
አሁን በሚገባ ከተዘናጋችሁና ወደ ወሬው መሐል ከገባችሁ ዘንዳ ወደ ሳሲት ወግ እንምጣ፡፡ ከገጠርና ከተማ የቱ ይሻላል ከሚለው ወጥተን የገጠር ከተማ ላይ ሕይወት ከመዝናናት አንጻር ምን ይመስላል ወደሚለው እንምጣ፡፡
ሳሲቶች በምን ይዝናናሉ ስንል እንደየወቅቱ ሁኔታ፣ እንደ ሰውየው ወይም ሴትዮዋ የዕድሜ፣ የሃብት፣ የጾታ ሁኔታ ወዘተ ይለያያል፡፡ የቅዳሜ ገበያ ድብድቦችና ትዝታዎቼ የሚለውን ጽሑፌን መለስ ብላችሁ ብታዩ ቅዳሜ ምን ያህል ሰው የሚዝናናባት አንደሆነች ትገነዘባላችሁ፡፡ ከቴፑ ሙዚቃው ሲንቆረቆር፣ የመኪናው ጡሩምባ፣ የሰዉ ሁካታ፣ የግርግሩ አጠቃላይ ሁኔታ ያቺን የቀዘቀዘች ከተማ ሲያደምቃት በቅዳሜ ገጽታ መዝናናታችሁ የማይቀር ነው፡፡ ልዩ ልዩ ትዕይንት አለ፡፡ ከዚያ እየመረጡ መኮምኮም ነው፡፡ ቅዳሜ ወሬ ልይ ብሎ ለመዝናናት የሚወጣው ሰው ብዙ ነው፡፡ ጠጅ ቤት ጎራ ማለት፣ ብርዝ በዲፎ ዳቦ መብላት፣ ጠላ መኮምኮም፣ ለስላሳና ቢራ ማንቆርቆር፣ ሻይ ፉት ማለትም ይቻላል፡፡ አረቄን አልረሳሁም፡፡ ኮበሌ አቅፎም ባይሆን ጎን ለጎን ሆኖ መንሸራሸርም ይቻላል፡፡ ጠጅ ቤትን ካነሳን የክንፈ ጠጅ ቤት አለ፡፡ የከተማችንን ታዋቂ ሰው ማለትም በከተማው ፒያሳ ላይ ሰፊ ግቢ ያላቸውን የጋሽ ኪዳኔን ልጅ ነው ያገባው፡፡ በደርግ ጊዜ እነ ጋሽ ወጋየሁም ጠጀ ቤት ነበራቸው አሉ፡፡ አልደረስኩበትም፡፡ ሌላው ታዋቂ ጠጅ ቤት ዘቦንቻው ጠጅ ቤት ሲሆን ባለቤቱ ከአዲስ አበባ ወይም ከአንድ ትልቅ ከተማ የመጡ የተማሩ ሰው ናቸው፡፡ እደጅ ቁጭ ብለው የእንግሊዝኛ መጻሕፍትን በትርፍ ጊዜያው ሲያነቡ አያቸዋለሁ፡፡ ከከተማ የወያኔ ፓለቲካ ያባራቸው ወይም ተጉለቴ ዝርያቸው ወደ ሳሲት ይግፋቸው አላውቅም፡፡ ጥናት እያደረጉም ይሆናል፡፡ ‹‹እናንተ፣ እዚህ ቅንጅት ቅንጅት ስትሉ ኦነግ እንዳይገባላችሁ!›› እንዳሉኝ እንደ ጋሽ ልጃምባው ሁሉ በፖለቲካ የነቁ ተጉለቴ ከተምኛ ጎብኛችን ይሆናሉ፡፡ በየገባችሁበት ጠጅ ቤት አሸናፊ ወርቅሸትንም ሆነ አባቱን ወርቅሸት ተክሌን ማግኘታሁ አይቀርም፡፡ ደግ ስለሆኑ ይጋብዟችኋል፡፡ ሳቃቸው በተለይ አይረሳም፡፡
በበዓላት ያለው መዝናኛ ልዩ ነው፡፡ የፋሲካ ሩር ልገታና እሱን የሚከተለው ከኳስ ሜዳ እስከ ዥንጎዶ ተራ አቧራ የሚያጨሰው ጭፈራ አለ፡፡ ሴቶቹም ከበው ስምንት ቀን ይጨፍራሉ፡፡ ቡሄ፣ እንቁጣጣሽ፣ መስቀል፣ ገና፣ ጥምቀት አሉ፡፡ የየአካባቢው አገር ንግሥም አይረሳም፡፡ ዘመድ መጠየቂያና ልዩ መዝናኛ ነው፡፡
ዘመን አመጣሽ መዝናኛዎችም አሉ፡፡ ጆተኒ፣ ቴኒዝ፣ ሙዚቃ፣ በእጅ ተይዛ ሁለት ዓይን ላይ ተደርጋ የምትታይ ፊልም፣ ኋላ የመጣውና ሙሉ ታሪኩን የጻፍኩለት ቴሌቪዥን አይረሱም፡፡ ቴፕ ወይም ሬዲዮ ያላቸው ወደ ሃብታምነት የተጠጉ ናቸው፡፡ በቴፕ የአስቴር አወቀን ሙዚቃ የሰማ ከሳሲት በታች ያለ ገጠር ውስጥ ያደገ ልጅ አንዲት ሴትዮ ብቻዋን አውራጅም ተቀባይም መሆኗ አግራሞት አንዳጫረበት ነግሮኛል፡፡
ጠላ ጠጥቼ የሰከርኩት አስረኛ ክፍል ሆኜ ግዛው ጌታነህ ጋብዞኝ ነው፡፡ ሌላ የሚያካሂደው ሰው አጥቶ የጋበዘኝ ግዛው ና አጫውተኝ ብሎ ወስዶኝ ነው፡፡ ሁለት ሽክና ጠላ አስክሮኝ ሌላ ዓለም ውስጥ ገባሁ፡፡
ሳሲቶች ስራ ከሌለባቸው ጠዋትና ማታ ፀሐይ እየሞቁ ተሰብስበው ማውራት ልማዳቸው ነው፡፡ ቀንም ቢሆን እቤት ወይም ጥላ ቦታ ሆነው ማውራታቸው የተለመደ ነው፡፡ ዕለቱ ጠላ የተጠመቀበት ከሆነ ወደተጠመቀበት ቤተ ሄደው እየጠጡ ያወጋሉ፡፡ ውርርድ ይወራረዳሉ፡፡ ጨዋታ አዋቂዎች ይጠራራሉ፡፡ ጓደኛሞች ይገባበዛሉ፡፡ ስራ እየሰሩ ማለትም ሴቶቹ ስፌት እየሰፉ፣ እህል እየለቀሙ፣ ምግብ እያዘጋጁ ይጨዋወታሉ፡፡
ትምህርት ቤት ግቢ ወይም ምድርኮሶ ሄደው ስፖርት የሚሰሩ ወይም የእግርኳስና የመረብኳስ ግጥሚያ የሚያዩ አሉ፡፡ ዓመታዊ የትምህርት ቤቶችን ውድድር ማየቱም አስደሳች ነው፡፡ ሩጫ፣ ዝላይ፣ ኳስ አለ፡፡ አዝናኝ ውድድሮችም እንዲሁ፡፡ የሞጃ ህዝብ የሚገናኝበት ነው፡፡ እኛ አንዲት አንድ ብር በነፍስወከፍ የምናዋጣባት የእግርኳስ ክበብ ነበረችን፡፡ አባላችን ጌትሽ ጠብቄ ወደ ሀረር ወይም ሌላ ከተማ ሄዶ ናፍቀነው ደብዳቤ ልኮልን ተሰብስበን ተነቦልናል፡፡
ትልልቅ ሰዎች ሲሰበሰቡ ሁልጊዜ ወሲብ ተኮር ወሬ የሚያወሩ አሉ፡፡ በቀልድና ጨዋታ አዋቂነታቸው የሚፈለጉ ደማሞች አሉ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ጨማምሩበት፡፡