እሑድ 17 ሜይ 2026

ሕይወት ከእገታ ማስጠንቀቂያው በኋላ

 ሕይወት ከእገታ ማስጠንቀቂያው በኋላ

‎ግንቦት 10፣ 2018 ዓ.ም.

መዘምር ግርማ

‎ደብረብርሃን

 

 

‎

‎ሚያዝያ 26፣ 2018 ዓ.ም. ምሽት የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ደረሰኝ። ከፖለቲካ ጋር ለማነካካት የሞከረ ይመስላል። በሁለት ቀናት ውስጥ ዋጋዬን እንደሚሰጡኝም የሚገልጽ ዛቻ ነበረበት። እንደዚህ ዓይነት ነገር ገጥሞኝ ስለማያውቅ ተደናገጥኩ፡፡ ከጓደኛዬና ከልጁ ጋር በአንድ ካፌ ነበርኩ፡፡ ሃሳቤ ወደ ማስጠንቀቂያው ስለነበር በደንብ ለማውራትም አልቻልኩም፡፡ ማታ አስብበታለሁ ብዬ ትንሽ የእግር ጉዞ ስናደርግ አምሽተን ወደ ቤት ገባሁ፡፡

‎በማግስቱ ጠዋት ተዛማጅ ማስጠንቀቂያ በስልክ ከሌላ ቁጥር ደረሰኝ። ከደብረብርሃን ከተማ ዉጪ አታክልት በተባለ ቦታ እንድገኝ የሚያሳስብ ነበር። አታክልትንም አላውቀውም መሄድም አልፈልግም፡፡ የሚያስኬደኝም ምክንያት አልነበረም፡፡ ግለሰቡ ሲደውል ስሜ ነው ያለውንና በቴሌግራምና በትሩኮለር አካውንቱ የጻፈውን ስም ለማጣጣም ሞክሯል። ያናገረኝ አንድ ሰው ቢሆንም እኛ እያለ ይናገራል፡፡

‎ሁኔታው አሳሳቢና አስደንጋጭ ነበር። ሁልጊዜም እንደማደርገው ግን ደብረብርሃንን ትቼ የትም ላለመሄድ ወሰንኩ። ባለፉት አስር ዓመታት በነበሩት ቀውሶች እዚሁ ነኝ። የፖለቲካ ቀውስ በዜጎች ላይ ብዙ ችግሮችን እንደሚጋብዝ አውቃለሁ። ከአስተዳደግም ቢሆን በ1983 በነበረው የመንግሥት ለውጥ ወቅት አጋጣሚውን በመጠቀም ንፁሃን እንደተጎዱ ስሰማ አድጌያለሁ። ከንባቤም እንዲሁ። በዓለም ታሪክ፣ በአፍሪካ፣ በአገራችን ሁሉ የደርግ ጊዜውን ጨምሮ ዜጎች የምክንያት አልባ ጥቃት ሰለባዎች ነበሩ። በእንደዚህ ዓይነት ጊዜዎች ነው የሰላምን አስፈላጊነት የምንረዳው፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት ህወሃት በመንግስት ላይ በከፈተው ጦርነት ወቅትም አስጊ ሁኔታ አሳልፈናል፡፡ በሕይወት ለመቆየታችንም ሆነ አገራችን ስለመቀጠሏ ዋስትና አልነበረንም፡፡ በወቅቱ ደብረብርሃን ቆይቼ ብዙ ነገር አይቻለሁ፡፡ ያየሁትንም ጽፌ በማህበራዊ ሚዲያ ሳስተላልፍ፣ ካለሁበት ሆኜ በሚዲያም ቃለመጠይቅ ስሰጥ ነበር፡፡ በሌሎች ግጭቶች ወቅትም ያየሁትን እጽፋለሁ፡፡ ተንኮለኛ ከመሰሉኝ ሚዲያዎች ውጪ ለደወሉልኝም አውርቻለሁ፡፡

ወደቅርቡ ክስተት ስመለስ በቀጣዩ ቀን የባንክ አካውንት በሌላ ቁጥር ተልኮ በዚያ አካውንት እንዳስገባ ተጠየቅሁ። ከቀደሙት ቀናት ጥሪዎች ጋር ይያያዝ አይያያዝ እርግጠኛ አይደለሁም። የሙስሊም ሴት ስም ነበር። ወደ ባንኩ የጥሪ ማዕከል ስደውል ለፖሊስ ሪፖርት እንዳደርግ መከሩኝ።

‎ስልኮቹን ለወዳጅ ዘመድ በትኜ ሳጣራ ቀደም ሲል ገምቼ እንደነበረው ሁሉ የተፈለግሁት ለፖለቲካ ዓላማ ላይሆን እንደሚችል ስለተረዳሁ የመፍትሔ እርምጃዎችን ቀየስኩ። አንዱ ጉዳዩን ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ማውጣት ነበር። የጠየቅኋቸው ጋዜጠኞችም አሉ። ያወያየኋቸው ጓደኞችም እንዲሁ። ‎አንድ ሰው በፌስቡክ ያገኙትን ልጥፌን በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ቴሌግራም ቡድን ሲለጥፉት ጠያቂዬ ብዙ ሆነ። ‹‹ማንንም እንዳታምኑ!›› በሚለው የነጻነት ወርቅነህ ንግግር መሰረት እንኳን ሰውን ጥላዬን አላመንኩትም ነበር፡፡ ሰላም ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑ የበለጠ ገባኝ፡፡ ስብሃት ገብረእግዚአብሔር እንዳለው ጦርነትን ፍራቻ መሯሯጥ ሳይኖር ማን ምን የለኛል ሳትል በሰላም ወጥቶ መግባት ትልቅ ነገር ነው፡፡

 

‎በቀጣዩ ቀን ለፖሊስ ሪፖርት አደረግሁ። የስልክና የጽሑፍ ማስጠንቀቂያው ከየት አቅጣጫ ሊመጣ እንደቻለ አልተረዳሁም። በግል ፀብ፣ ለማስጨነቅ በማሰብ ወዘተ ተደውሎልኝ ሊሆን ይችላል። በአንዳንድ የበጎ አድራጎትና የንባብ ሥራዎች ላይ ስሰማራ ገንዘብ የተረፈኝ የሚመስለው ሰውም ይኖራል። ‎ከክስተቱ ጥቂት ቀናት በፊት የጽሑፍ አርትዖት ካላደረክልኝ ብሎ መጥፎ የጽሑፍ መልዕክት ከላከልኝ ወጣት ዉጪ በቅርቡ ምንም አላስታውስም። ‎በዓሉ ግርማ አንድ ወቅት ከጓደኛው ጋር በአንድ ካፌ ሲያወራ አንድ ጥቁር መነጽር ያደረገ ሰው መጥቶ ይለምነዋል፡፡ በዓሉም ለዚያ ሰው ሳንቲም ይሰጠዋል፡፡ ሰውዬው ከሄደ በኋላ ሰውዬውን እንደሚያውቀው በዓሉ ለጓደኛው ይነግረዋል፡፡ ‹‹ታዲያ ለምን ሰጠኸው›› ብሎ ለጠየቀው ጓደኛው የበዓሉ መልስ ‹‹ሌላ የማላውቀው ሰላይ እንዳይመድቡብኝ›› የሚል ነበር፡፡ እኔ እንደ በዓሉ ታዋቂ ተፈላጊ ዒላማ ባልሆንም የማውቃቸው ተንኮለኞች ግን በዙሪያዬ አሉ፡፡ መኖራቸውን እያወቅሁ ዝም እላለሁ፡፡ የማውቀው ስለ አድራታቸው ከወዳጅ ዘመድ ማስጠንቀቂያ ስለሚደርሰኝና በራሴ መንገድ ስለምደርስበት ነው፡፡ ከዚህ ዉጪ በርካታ አበረታች ወዳጆች ያሉኝ ሰው ነኝ፡፡ ለማንኛውም ዜጎች ይህን የመሰለ ችግር ሲገጥማቸው በሚመለከተው አካል በኩል መደረግ ያለበት እገዛ ይኖራል ብዬ እገምታለሁ። ተመሳሳይ ዛቻና ማስጠንቀቂያ የደረሳቸው እንዳሉ ከጓደኞቸም ሆነ ወዳጅ ዘመዶቼ ተረድቻለሁ። በሃብትም ሆነ በስራቸው ለከተማችን አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ሰዎች እንዳይበረግጉ የህግ ከለላ ያስፈልጋቸዋል፡፡

‎ችግሩ የሚያሳስብ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ብቻ ሳይሆን አኗኗራችንን፣ አዋዋላችንን ወዘተ እንድናስተካክል የሚያስገድድና የሚያሳስብ ሁኔታ ይኖር ይሆናል።  

‎የምኖርበት ቦታም ሆነ አገራችን ለደህንነት አስጊ እንደሆነ እረዳለሁ። ይሁን እንጂ ወደ ሌላ ቦታ ልቀይር የምችል አይመስለኝም።

‎"አዲስ አበባ እኔ ቤት ና"፤ "ናይሮቢ ብትመጣ መሳፈሪያ እንጂ የማረፊያ ቤት ሃሳብ አይግባህ" ያላችሁኝን ወዳጆቼን አመሰግናለሁ። "ለማንበብና መጻፍ ስራ እንድትመጣ ተመካክረን እንነግርሃለን" ያሉኝ የአንድ ፋውንዴሽን ሰዎችም አሉ። ከተስማሙ ይጠሩኝ ይሆናል። ቢሳካ በክረምት እረፍቴ ለአንድ ወይም ሁለት ሳምንት ካልሆነ በቀር ከዚህ ለረዘመ ጊዜ የምሄድ አይመስለኝም።

‎ማስጠንቀቂያው ሌሎችም ኪሳራዎችን አምጥቶብኛል። በሌላ ቀን እመለስበታለሁ። በገንዘብ ረገድ የመንግስት ሰራተኛ መሆኔ ይታወቃል። ከመጽሐፍ ሕትመትና ከጽሑፍ ሥራ ያገኘሁትንም ገንዘብ ለራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት ማደራጃ አውያለሁ። በአሁኑ ሰዓት ቤተመጻሕፍቱ አድራሻ መቀየሩን ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ገልጫለሁ። ቤትም መኪናም የለኝም። አልፈልግምም። የቅርብ ሰዎቼና ባልደረቦቼ ይህን ሁሉ ያውቃሉ። "ሌባ እናት ልጇን አታምንም" የሚለውን ተረት ሚነግረኝ ወዳጄ የለኝምም ሆነ አልሰርቅም ብትል አያምኑህም ይላል። "የገንዘብን ከንቱነት የሰበከ" የሚል ማዕረግም ጨምሮልኝ ነበር። አስተያየትና ከሰጡኝና አይዞህ ካሉኝ ሁሉ ‎ሁለት ወዳጆቼ በኤክስ መድረክ በጉዳዩ ላይ ለጻፍኩት የሰጡኝና የተመላለሱት የሁኔታውን አሳሳቢነት ያሳያል።

‎አንዷ "ከዚያ ውጣ።" ብለው ጻፉ።

‎"የት ይሂድ?" ብለው ሌላው መለሱላቸው። እኔም መሄጃ እንደሌለኝ ጨመርኩበት።

‎ምን ተፈልጎ ወደኔ እንደተመጣ አላውቅም።

‎እስኪ አስተያየት ስጡበት። በዚህ ጽሑፍ ላይ ምን ይጨመር? ሌሎች ተመሳሳይ ችግር እንዳይደርስባቸው ምን ዓይነት ቅድመጥንቃቄ እናድርግ? ከማን ምን ይጠበቃል?

‎አንድ የሕግ ባለሙያ ወዳጄን አማክሬ የጻፍኩት ነው። ሌሎችን ለማስተማርና ለጥንቃቄ ይሆናል ጻፈው ብሎኝ ነው።

‎ሁላችሁንም አመሰግናለሁ!


ዓርብ 17 ኤፕሪል 2026

የተገለጠላችሁ መቼ ነበር?



አንድ ክህሎት ወይም ትምህርት ሲገባችሁ የተለየ ስሜት አለው። አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አብሮኝ የተማረ ጓደኛዬ እንግሊዝኛ አራተኛ ክፍል ሆኖ እንደገባው ነግሮኝ ነበር። ገባኝ የሚለውም ልክ እንደ አማርኛ መነጋገሪያ መሆኑ ስለገባኝ መነጋገር ጀመርኩ አለ። በትምህርት ቤታችንም ብቸኛው እንግሊዝኛ ተናጋሪ ተማሪ ነበር ለማለት እደፍራለሁ። አስራአንደኛ ክፍል ሆኖ ደግሞ ኢኮኖሚክስ አንድ ምሽት እንደተገለጠለት ነግሮኛል። የተገለጠለትም ሌሊቱን መጽሐፉን በማንበብ ነው። መምህር ጓደኛዬ የተፈጥሮ ሳይንስ ትምህርቶችን ከአካባቢው ካሉ ሁነቶችና የፋብሪካ ምርቶች አንፃር በማገናዘብ እንደተረዳቸው አውግቶልኛል። ሌላው መምህር ደግሞ ሥነጽሑፍ የገባው በመጀመሪያ ልቦለዶችን እንደ እውነተኛ ታሪክ አንብቦ ለጓደኞቹ በመተረክ እንደነበር ነግሮኛል። ስምንተኛ ክፍል ሲደርስ አብዛኞቹን ታዋቂ የአማርኛ ድርሰቶች አንብቧል። 

እናንተም አንድ ነገር የገባችሁን ጊዜ አስታውሱ። ይህን ያህል ውስብስብ አንደለም። ቴኒስን ለመቻል ዓይንህን ከኳሷ ላይ ሳትነቅል ተጫወት እንደተባለው ነው። ከአንድ ፊልም እንዳየሁት። ባያያዝኩት የልጆች መጽሐፍ የሽፋን ገጽ የሚታየውም ልጅ ተቀራራቢ ታሪክ አለው። ለመጀመሪያ ጊዜ ማንበብ ችሎ ወደ ቤት ይመለሳል።  ማንበብ መቻሉን ለቤተሰቦቹ ለማሳየት ሲሞክር ስራ ይዘዋል። ስለሆነም ለራሱ ማንበብ ጀመረ። ለመጀመሪያ ጊዜ ሳይጮህ ማንበብ የቻለው ሰው ከሺዎች ዓመታት በፊት በአንድ ቦታ መሆኑን ከአንድ መጽሐፍ አንብቤያለሁ። የመጀመሪያው መገለጥ ነው። ድምፁን ለሰው ባያሰማም በጉሮሮው በውስጡ እያነበበ ነበር። በጉሮሮ ወይም በድምፅ ማውጫ ክሮች (vocal cords) ምንም ድምፅ ሳያሰሙ በፍጥነት ማንበብን በርካቶች ለመጀመሪያ ጊዜ አግኝተነዋል ቢሉም ከመጀመሪያዎቹ አንዷ ኤቨሊን ውድ ነች። እኔም ያገኘሁት ወይም በፍፁም ፀጥታ ማንበብ የቻልኩ ጊዜ እንደ ትልቅ ግኝት ነበር ያየሁት። በእውነትም ነው። ዕድሜ ዘመናችንን ስናነብ የኖርን ሰዎች ምን አዲስ ነገር ልታስተምረን ነው ለሚሉ ምላሼ ትናንት ያጋራሁት ፕሮፌሰሮች ማንበብ እየተማሩ መሆኑን የሚያሳየው ዜና ነው። ልክ እንደ ተች ታይፒንግ ሁሉም ሊለማመደው የሚችለው ክህሎት ነው። በመጀመሪያዎቹ ጥቂት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ዓመታት ከምንማረው ሌላ ይህ ነው የሚባልና ተጨባጭ ልዩነት የሚያመጣ የንባብ ትምህርት እንዳልተማርን ጥናቶች ያሳያሉ። ታዲያ እንደዚህ ከሆነ ለምን በሰፊው በሥርዓተትምህርቱ ውስጥ አልተካተተም የሚልም አይጠፋም። በዚህ ጉዳይ ላይ ጆርጅ ስታንክሊፍ ጽፏል። እናንተን የፍጥነት ወይም የፀጥታ ንባብ ካስተማሯችሁ ከምታመጡት አዲስ ፍጥነት እኩል ሄደው ማስተማር አይችሉም የሚለውን ጨምሮ ሃሳቦችን ሰንዝሯል። በጉዳዩ ላይ በርካታ መጻሕፍት አሉ። ድረገፆችም ሆኑ መተግበሪያዎች አሉ። የሥልጠና መርሐግብሮችም እንዲሁ። እኛም አገር መተዋወቅ ይኖርበታል በማለት በአካባቢዬ ባሉ ትምህርት ቤቶችና አብያተመጻሕፍት ሥልጠናውን እየሰጠሁ ነው። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ይህን መንገድ ለሌሎች ለማሳየት በመጣር ላይ ነኝ። ኑ! በፍጥነትና በፍፁም ፀጥታ እናንብብ። በዚህ የቴሌግራም ቡድን እንገናኝ።

https://t.me/+YzM4zraPzGcyYTM0

እሑድ 8 ማርች 2026

From my diary

 “Are all of these professors?”

“You’re not really busy. You do nothing!”

These two statements were made by two American volunteers who were working in North Shewa. I came across them today while reviewing a file from 2015.

The first volunteer was surprised to see many lecturers sitting in the sun at a café housed in a tent. One day she also commented, “This looks like a boys’ club” after noticing that there were no female teachers in the staff lounge. The second comment was made by another volunteer who observed how we spent our days idly.  It seems like the same situation is occurring today. If universities are as such imagine what is going on elsewhere in other industries. 

One of them used to constantly correct my English, but I stubbornly refused to stop using inappropriate words and grammar. I even tried to provide evidence from books I had read. One day she insisted I should say ‘storage room’ instead of ‘store,’ but I disagreed. She pointed to the books on my table and said, “Just because it’s published, doesn’t mean all this shit on this table is correct.”

 

ቅዳሜ 21 ፌብሩዋሪ 2026

ሰቆጣ

 

የሰቆጣ ሰዎች በድርቅ ምክንያት በ2008 ዓ.ም. ተፈናቅለው ደብረብርሃን እንደመጡ አንዷ ተፈናቃይ የነገሩኝን ከቆየ ማስታወሻዬ አገኘሁት፡፡

‹‹ክረምት ሲመጣ ተበዳድረን ነው፡፡ ሐብታም የሆነ ችግርን ሊገፋው ይችላል፡፡ የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ክፈሉ ይሉናል፡፡ እኛ ግን የሚከፈል የለንም፡፡

እርዳታው ከመንግስት ይወጣል መሰል፡፡ ለእኛ ግን አይደርሰንም፡፡

እርዳታ እንደሚያስፈልግ ያወቅነው በሰኔ ነው፡፡

ከመምጣታችን በፊት ከብቶቻችንን አርደን በላን፡፡ የሚጠጣ ውሃ የለም፡፡

እዚህ መጥቼ ቁጭ ብዬ እስከ 7፡00 ድረስ አለቀስኩ፡፡ ወንድሜ ‹ምን አባሽ ያነፋርቅሻል! ሄደሽ እንሰዉ አትለምኚም እንዴ!› አለኝ፡፡ አገሬ ልሂድ ብለው ‹እንዴት አድርገሽ? 300 ብር ከየት ታመጫለሽ?› አለኝ፡፡

አገሩ አዝመራው ጥሩ ነው ስንባል ጊዜ ወደዚህ ወደ ደብረብርሃን መጣን፡፡

ብርድ ሞትን እዚህ፡፡››

አሁንም አሉ፡፡ መፍትሔ ቢፈለግላቸው ጥሩ ይመስለኛል፡፡

 

ዓርብ 20 ፌብሩዋሪ 2026

ቲፕ ውዴታ ወይስ ግዴታ?

 የቲፕ ሃሳብ የመጣው ከዉጪ አገር ይመስለኛል። ሦስት ዉጪ አገር የኖሩ ሰዎች ያወጉልኝን ወይም የጻፉትን ላጋራችሁ።



‎ሀ. አንድ ሰው ያወጉልኝ፦ አንድ ቦታ ዕቃ ገዝቼ ዋጋው 99 ሳንቲም ስለነበር 1 ሳንቲሟን ትቻት ሄድኩ። ባለ ሱቁ ጠርቶ መልስህን ውሰድ አለኝ። ተወው አልኩት። እሱም ተገረመ። ከአስተያየቱ እናንተ ጥቁሮች የማታድጉት ገንዘብን ስለማታከብሩ ነው የሚል ነገር ተረዳሁ።
‎ለ. ሌላዋ ደግሞ፦ አስተናጋጅ ሆኜ ሰርቻለሁ።  ሳስተናግድ ሂሳቡን ብቻ ከፍሎ ሊሄድ ቢሞክር ቲፔስ? እለዋለሁ። አንድ ምግብ ዋጋው አስር ዶላር ቢሆንና እኪሴ ያ ገንዘብ ብቻ ካለኝ ገብቼ አላዝም። ምክንያቱም ቲፕ የምሰጠው የለኝም።
‎ሐ. ሌላው የነቢይ መኮንን መጽሐፍ ላይ ያነበብኩት ሲሆን ደሞዝ የማይከፍሉና በቲፕ ብቻ የሚያኖሩ ሆቴሎች በአሜሪካ መኖራቸውን አንዷ አስተናጋጅ እንደነገረችው የጻፈበት ነው።
‎መ. በቲፕ ጉዳይ ላይ ተከራክረንበትም እናውቃለን። 'A Christmas Carol' የተባለውን ድርሰት ያነበብን ሰሞን ጎራ ለይተን ተከራክረናል። ጥገኝነትን ያመጣል ያልን ነበርን። ለሚሰሩ ሰዎች እገዛ ማድረግ ጥሩ ስለሆነ ይበረታታል ያልንም እንዲሁ።
‎አሁን አሁን ግን የዉጪው ባህል ጥንቅቅ ብሎ ገብቷል። ለተስተናጋጅ ብጥስጣሽ ብሮችን መመለስ ተለምዷል። እነዚያን ብሮች ባለታክሲ አይቀበላችሁም። ሌላም ቦታ አይሰሩም። አንድ ቀን ቲፕ ሰጥቶ በቀጣዩ ቀን መዝለል አይቻልም። ዓይን ያወጣ ብልጣብልጥነት ሰፍኗል። ትኩስ ነገር አዛችሁ መቶ ብር አውጥታችሁ ጠረጴዛ ላይ ስታስቀምጡት ይወስዷትና መልሱ በዚያው እንዲቀር ይፈለጋል። ይህን ጉዳይ ባለሃብቶቹ ይወቁ አይወቁ አናውቅም።
‎እናንተስ ምን ገጠማችሁ?
‎ሃሳቡን ትጋሩታላችሁ?

ማክሰኞ 10 ፌብሩዋሪ 2026

ዉሻና ሰው

 ‎ዉሻና ሰው

‎ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ዉሾችን አስመልክቶ እየተካሄደ ያለ ዘመቻ መኖሩን በማህበራዊ ሚዲያ እንመለከታለን። ዉሾቻችን ተገደሉበትን ያሉ ሰዎች እያለቀሱ የለቀቋቸው ቪዲዮዎች ታይተዋል። ንፍሮም የታየበት ቦታ አለ። ይህን የዉሾችን መግደል የተቃወሙ እንዳሉ ሁሉ ያፌዙበት ወይም ያቃለሉት አሉ። ለምን ታፌዛላችሁ ብለውም የተቆጡ የዉሾች ባለቤቶችና ደጋፊዎቻቸው ቁጣቸውንና ስድባቸውን አውርደዋል።

‎በዚህ አጊጣሚ አንዳንድ ነጥቦችን እናንሳ። እንደ ህብረተሰብ የራሳችን ዉሻ የሚኖረን ጊዜ አለ። ቤት ጠባቂ ነው። በቂ ምግብ ላይሰጠው ወይም እንክብካቤ ላይደረግለት ይችላል። የሌላን ሰው ዉሻ ግን በፍርሃት እናያለን። አሳደንም በድንጋይ እንመታለን። እኔም የተለየሁ አይደለሁም። ሳሲት ሳድግ አንዲት የጋሽ ማንደፍሮ ዉሻ ነክሳኛለች። የነከሰችኝ ትምህርት ቤት ውስጥ ሙጃ ቆርጬ ላመጣ ስሞክር የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነበር። ከትምህርት ቤታችን ጎን ባለው ክሊኒክ ታከምኩ። ያከሙኝ የሐኪም ቤቱ ዘበኛ ጋሽ አድማሱ ነበሩ። ሌላ ቀን ለሥራ ዘመቻ ወደ ችግኝ ጣቢያ የትምህርት ቤቱ ተማሪዎች ስንሄድ መንገድ ላይ አንድ ዉሻ ያልፍ ነበር። በርካታ ተማሪዎች በድንጋይ መቱት። ደሙ ፈሶ ሞተ። ተዉ ያለ መምህር አልነበረም።

‎ሌላ ቀን አንድ አሜሪካዊ በአገራቸው የዉሻ ዋጋ እስከ 5,000 ዶላር እንደሚደርስ ነገሩኝ። ጉግል ሳደርግ ልክ ነው። ከእኛ አገር የበሬ ዋጋ በለጠ። የዉሻና ድመት ምግብ ከሱፐርማርኬት የሚገዛ ሲሆን በዓመት እስከ 68 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል። በአንድ ወቅት ያየሁት የአውስትራሊያው የዉሻና ድመት ምግብ ከወቅቱ የኢትዮጵያ በጀት ይበልጥ ነበር።

‎በአገራችንም በሠይፉ ሾው የቀረበውን ዉሻ አርቢ አይተናል። ዉድ ዉሾችን ከዉጪ ያስመጣል። ያሳድጋል። ያረባል። ይሸጣል። የዉጪ ዜጎች በአዲስ አበባ በተባለው ቡድንም ውስጥ በመኪና የተገጨ የጎዳና ዉሻ ሲኖር ጠቁሙኝ እያለ ሲጠቆም ሄዶ የሚያክምና በዚያውም ማስታወቂያ የሚሰራ ሐኪም አለ። በቅርቡ በቲክቶክ ያየናት አንዲት ባለዉሻ በቀዶ ሕክምና ወቅት ማደንዘዣ አሰጣጡን አሳስቶ ዉሻዬን ገደለብኝ ስትል ያቀረበች ሴት አይተናል። ዶክተሩም ይቅርታ ጠይቆ ቪዲዮ ለቋል። ሥራው ስለሆነ ስሙን ማደስ ስለላበት ነው። ለዉሻቸው ከልኳንዳ ስጋ የሚገዙ እንዳሉ እናውቃለን። ደብረብርሃንም አንድ ሰው ነበር። ወገኖቼ ይህ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች ወግ ነው። ከአንድ ዶላር በታች ዕለታዊ ገቢ አለው የሚባለው ብዙኃን ኢትዮጵያዊ በዚህ የቅንጦት ሕይወት ላይ ጥያቄ ቢያነሣ ማንም አይሰማውም። ጉዳዩ አከራካሪ ነው። ክርክሩ ከአፄ ኃይለሥላሴ ዉሻ ከሉሉ የጀመረ ነው። የወሎና የትግሬ ሕዝብ እፍኝ ጥሬ አሮበት በሜመዳው የአሞራ ሲሳይ ሆኖ ሳለ የአፄ ኃይለሥላሴ ዉሻ ሞቶ ሐውልት ተሰርቶለታል፤ ይለቀስለታል፤ በሚል የቀረበውን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘገባ ያስታውሷል።

‎በዘመነ ኢህአዴግም ሰልፍ ተከከክሎ ሳለ ሚሚ ስብሃቱ የተገኘችበት የእንስሳት መብት ሰልፍ ይታወሳል። ሰዎች ምግብ፣ ሰብዓዊ መብት፣ መጠለያ አላገኙም በሚባልበት አገር የተነሣ ጥያቄ ስለሆነ ነው የተወዛገበነው።

‎

እሑድ 8 ፌብሩዋሪ 2026

የትምህርት አቅጣጫ ወዴት ነው?

 የትምህርት አቅጣጫ ወዴት ነው?


ትምህርት አጉል አቅጣጫ እየሄደች ይመስላል። ለዚህ ማሳያ የተወሰኑ ክስተቶችን ላንሳ። ከሰሞኑ አንዲት መምህር እያስተማረች የነበረበት ክፍል ለፈተና ተፈልጎ እንድትወጣ ስትጠየቅ በጥያቄው ተስማምታ ስትወጣ አየኋት። አንዱ ተማሪ ዲቫይደሯን፣ ሌላኛው ፕሮጀክተሯን ይዘውላት  ይሄዳሉ። አንዳቸውም ደብተር አልያዙም። የያዙትን ለመገመት አትቸገሩም - ስማርት ስልኮችን ነው። ከሁለት ዓመታት በፊት የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነጽሑፍ ተማሪዎች ነበሩን። ሳስተምር ሰሌዳውን ፎቶ ያነሱታል። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሆነ ሰነድ ምናልባት የክፍለጊዜ ድልድል ሊያሳዩኝ ስልኮቻቸውን ሲከፍቱ የምናስተምራቸው መምህራን ሰሌዳው አጠገብ ቆመን ያነሱን ፎቶዎች አሉ። እኔ ማክሰኞና ሐሙስ ክፍለጊዜ ቢኖረኝ የአንዱን ሳምንት ጽሑፌን ከሌላው እንዴት እንደሚለዩት ግራ ይገባኛል። ከኔ በፊት ወይም በኋላ ያስተማሯቸውንስ? ነገሩ ግራ ይገባል። በፕሮጀክተር የሚያስተምሩ መምህራንን ፓወርፖይንት በስልካችን ይዘናል ብለው ደብተር የማይዙት የሌሎች ትምህርት ክፍሎች ተማሪዎችም ሆኑ እኛ የሥነጽሑፍ ተማሪዎች ደብተር አለመያዛቸው ምንም ምክንያታዊ ሆኖ አይታየኝም። መጻፍ የራሱ የሆነ ጠቀሜታ አለው። መምህራን ከፓወርፖይንት ዉጪ የሚያስተምሩት ነገር አለ። መጻፍ የመማር አካል ነው። አንዱን ትምህርት ከሌላው ለይተን ማስታወሻ መያዝ ይገባናል። ትምህርት ምን ዓይነት አጉል አቅጣጫ እየሄደ ነው? የትምህርት ዓላማ አእምሮን ማልማትና ችግርፈቺ ዜጎችን ማፍራት ነው። ሰናይ ተግባር የሚሰሩ ወጣቶችንም መፍጠር አለበት። ለዚህ ደግሞ ትኩረት ሰጥቶ ምንም ሳይሰስቱ መማር ተገቢ ነው። ዘመን አመጣሹ ቴክኖሎጂ በአሳይመንት፣ በንባብ፣ በፈተና፣ በምርምርና በሌሎችም የትምህርት ጉዳዮች እያመጣ ያለውን ችግር ትገምታላችሁ ብዬ አልነካካሁትም። ፈተናው እውነት ሀሰትና ምርጫ ሆኖስ ተማሪዎች ምን ያህል ለማሰብና ቤተመጻሕፍት ገብተው ከፓወርፖይንት በላይ ለማንበብ ይነሳሳሉ?

በማካካሻ (remedial) ፕሮግራም የሚባክነው የአገር ሀብት ሌላው ነው። ተሻለሎ ለማይሻሻል ክህሎት የተማሪዎች ዕድሜና የአገር ሀብት ይባክናል። በትምህርት ዘርፍ ማየት ያለብን በርካታ ጉዳዮች አሉ። 

የከተማ ልጆች በኮምፒውተር እየነተፈኑ የገጠሩ በወረቀት መፈተኑ ያመጣው ኢፍትሃዊነት ዘንድሮ ዩኒቨርስቲዎች ትምህርት ባስጠላቸው የከተማ ወጣቶች ለመሞላታቸው ምክንያት አልሆነ ይሆን?  ኮምፒውተሩ ፈተና የሚሰሩ ሶፍትዌሮች እንዳሉት የተፈተነ ተማሪ ነግሮኛል። እንወያይበት።

ምን ላንብብ? ክፍል 2

በክፍል አንድ ያየነውን የንባብ ወግ ዛሬ እንቀጥላለን፡፡ ምን ላንብብ ለሚሉ ወገኖች በርካታ ምላሾች ቢኖሩም ከዓመታት በፊት ሰዎች እናነባለን የሚሉበትንና የማልስማማበት ዓይነት ንባብ አንብቡበት ልላችሁ ነው፡፡ ይኸውም ሶፍት...