2023 ጁላይ 6, ሐሙስ

የሳሲት ወጎች ቁ. 13 ሳሲቶች በምን ይዝናናሉ?

 የሳሲት ወጎች

ቁ. 13

ሳሲቶች በምን ይዝናናሉ?

 

ገጠርን ስታስቡ ምን ይሰማችኋል? የመዝናናት ስሜት ይመጣባችኋል? ወይስ ይጨንቃችኋል? እስኪ በሁለት በኩል ሊነሱ የሚችሉ ሃሳቦችን እናንሳ፡፡

ገጠር እንደሚያስደስታቸው፣ እንደሚያዝናናቸውና ሰላም እንደሚሰጣቸው የሚናገሩ ሰዎች አሉ፡፡ ገጠር ከሁካታ የራቀ ሰላማዊ ቦታ ተደርጎ ይታያል፡፡ የአየሩ ንጽህና፣ የሰዉ የዋህነት፣ የህይወቱ ቀላልነት፣ የምግቡ ተፈጥሯዊነት ተደማምሮ ገጠርን የመሰለ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ቢል የለባችሁም፤ የቤት ኪራይ ደረሰ አትሉም፡፡ ነዳጅ አያሳስባችሁም፡፡ ምን ብዬ ልንገራችሁ? በተለይ በከተሜ ዓይን ሳየው ይህንን አያለሁ፡፡ ከዚህኛው የወንዙ በኩል ሆኖ ሲያዩት የዚያኛው በኩል የበለጠ ይጣፍጥ ይመስላል እንዲሉ ላሞች፡፡

ገጠር የሚያንገሸግሸው አለ፡፡ አንድ አጎቴ አለ፡፡ አደናውሰኝ ዘነበ ይባላል፡፡ አረም የሚያርምበትም ሆነ እርሻ የሚያርስበት ማሳው ዋሻ በተባለ ቦታ ይገኛል፡፡ ጠዋት የወጣ በዚያ በተራሮች በተከበበ ቦታ በሚገኘው ማሳው ላይ ሲሰራ ውሎ ማታ ሲመለስ ነው ሰው የሚባል የሚያየው፡፡ በጣም ይጨንቀኛል ይላል፡፡ ሌላ ቀን እናቴ ለምናው ከሳሲት ወደ ሰላድንጋይ ከሚወስደውና ወስዶ ከሚመልሰው መኪና መንገድ ዳር ባለው መሬቷ ላይ ሲያርሙ ይውላሉ፡፡ ከሰው ጋር እያወሩ ማረም የበለጠ እንደሚያስደስተው ነገራቸው፡፡ መንገድ ዳር በሚገኘው ማሳ ላይ በመዋሉም መንገደኞችንና መኪኖችን እያየ ይዝናናል፡፡ ከዚህች ንጽጽር እንኳን ስናይ ገጠር የሚያስጨንቀውና ከተማና የሥልጣኔ ትሩፋት የሚያስደስተው አለ፡፡

ገጠር የሚያስደስታቸው ለአንድና ሁለት ቀን የሆነም አይጠፉም፡፡ ዘመድ ለመጠየቅ፣ ለለቅሶ፣ ለሰርግ፣ ለንግሥ፣ ለመንፈሳዊ ጉዞ ወዘተ ብቅ ብለው የሚመጡ አሉ፡፡ ‹‹ክረሙ›› ብተሏቸው ‹‹ግደሉኝ›› ብለው ይቃወማሉ፡፡ ‹‹ልጄ፣ ሜስቴ፣ ዕቁቤ፣ ፓርቲዬ ብለው ልሂድ ይላሉ፡፡

ገጠር የሚያንገሸግሻቸው በአንዳንድ ሁኔታ እንጂ ከገጠር ስብዕና አይወጡም፡፡ የከተማ ሁካታ ሲሰማቸው መልሰው ያቺው ገጠሬ ይላሉ፡፡ ከላይ ያየነው አደናውሰኝ ስለ ሥልጣኔ ለማየት የቻለው ዘግይቶ ነው፡፡ የቄስ እንጂ የመንግስት ትምህርት አልተማረም፡፡ ሰላድንጋይን እንኳን በ30 ዓመቱ አየ፡፡ አዲስ አበባን ቢያይ መንግስተሰማያት ሊመስለው ይችላል፡፡ ቆይቶ ሲኦል ነው ሊልም ይችላል፡፡ ያብለጨለጨ ሁሉ ወርቅ አይደለምና፡፡

አሁን በሚገባ ከተዘናጋችሁና ወደ ወሬው መሐል ከገባችሁ ዘንዳ ወደ ሳሲት ወግ እንምጣ፡፡ ከገጠርና ከተማ የቱ ይሻላል ከሚለው ወጥተን የገጠር ከተማ ላይ ሕይወት ከመዝናናት አንጻር ምን ይመስላል ወደሚለው እንምጣ፡፡   

ሳሲቶች በምን ይዝናናሉ ስንል እንደየወቅቱ ሁኔታ፣ እንደ ሰውየው ወይም ሴትዮዋ የዕድሜ፣ የሃብት፣ የጾታ ሁኔታ ወዘተ ይለያያል፡፡ የቅዳሜ ገበያ ድብድቦችና ትዝታዎቼ የሚለውን ጽሑፌን መለስ ብላችሁ ብታዩ ቅዳሜ ምን ያህል ሰው የሚዝናናባት አንደሆነች ትገነዘባላችሁ፡፡ ከቴፑ ሙዚቃው ሲንቆረቆር፣ የመኪናው ጡሩምባ፣ የሰዉ ሁካታ፣ የግርግሩ አጠቃላይ ሁኔታ ያቺን የቀዘቀዘች ከተማ ሲያደምቃት በቅዳሜ ገጽታ መዝናናታችሁ የማይቀር ነው፡፡ ልዩ ልዩ ትዕይንት አለ፡፡ ከዚያ እየመረጡ መኮምኮም ነው፡፡ ቅዳሜ ወሬ ልይ ብሎ ለመዝናናት የሚወጣው ሰው ብዙ ነው፡፡  ጠጅ ቤት ጎራ ማለት፣ ብርዝ በዲፎ ዳቦ መብላት፣ ጠላ መኮምኮም፣ ለስላሳና ቢራ ማንቆርቆር፣ ሻይ ፉት ማለትም ይቻላል፡፡ አረቄን አልረሳሁም፡፡ ኮበሌ አቅፎም ባይሆን ጎን ለጎን ሆኖ መንሸራሸርም ይቻላል፡፡ ጠጅ ቤትን ካነሳን የክንፈ ጠጅ ቤት አለ፡፡ የከተማችንን ታዋቂ ሰው ማለትም በከተማው ፒያሳ ላይ ሰፊ ግቢ ያላቸውን የጋሽ ኪዳኔን ልጅ ነው ያገባው፡፡ በደርግ ጊዜ እነ ጋሽ ወጋየሁም ጠጀ ቤት ነበራቸው አሉ፡፡ አልደረስኩበትም፡፡ ሌላው ታዋቂ ጠጅ ቤት ዘቦንቻው ጠጅ ቤት ሲሆን ባለቤቱ ከአዲስ አበባ ወይም ከአንድ ትልቅ ከተማ የመጡ የተማሩ ሰው ናቸው፡፡ እደጅ ቁጭ ብለው የእንግሊዝኛ መጻሕፍትን በትርፍ ጊዜያው ሲያነቡ አያቸዋለሁ፡፡ ከከተማ የወያኔ ፓለቲካ ያባራቸው ወይም ተጉለቴ ዝርያቸው ወደ ሳሲት ይግፋቸው አላውቅም፡፡ ጥናት እያደረጉም ይሆናል፡፡ ‹‹እናንተ፣ እዚህ ቅንጅት ቅንጅት ስትሉ ኦነግ እንዳይገባላችሁ!›› እንዳሉኝ እንደ ጋሽ ልጃምባው ሁሉ በፖለቲካ የነቁ ተጉለቴ ከተምኛ ጎብኛችን ይሆናሉ፡፡ በየገባችሁበት ጠጅ ቤት አሸናፊ ወርቅሸትንም ሆነ አባቱን ወርቅሸት ተክሌን ማግኘታሁ አይቀርም፡፡ ደግ ስለሆኑ ይጋብዟችኋል፡፡ ሳቃቸው በተለይ አይረሳም፡፡

በበዓላት ያለው መዝናኛ ልዩ ነው፡፡ የፋሲካ ሩር ልገታና እሱን የሚከተለው ከኳስ ሜዳ እስከ ዥንጎዶ ተራ አቧራ የሚያጨሰው ጭፈራ አለ፡፡ ሴቶቹም ከበው ስምንት ቀን ይጨፍራሉ፡፡ ቡሄ፣ እንቁጣጣሽ፣ መስቀል፣ ገና፣ ጥምቀት አሉ፡፡ የየአካባቢው አገር ንግሥም አይረሳም፡፡ ዘመድ መጠየቂያና ልዩ መዝናኛ ነው፡፡

ዘመን አመጣሽ መዝናኛዎችም አሉ፡፡ ጆተኒ፣ ቴኒዝ፣ ሙዚቃ፣ በእጅ ተይዛ ሁለት ዓይን ላይ ተደርጋ የምትታይ ፊልም፣ ኋላ የመጣውና ሙሉ ታሪኩን የጻፍኩለት ቴሌቪዥን አይረሱም፡፡ ቴፕ ወይም ሬዲዮ ያላቸው ወደ ሃብታምነት የተጠጉ ናቸው፡፡ በቴፕ የአስቴር አወቀን ሙዚቃ የሰማ ከሳሲት በታች ያለ ገጠር ውስጥ ያደገ ልጅ አንዲት ሴትዮ ብቻዋን አውራጅም ተቀባይም መሆኗ አግራሞት አንዳጫረበት ነግሮኛል፡፡

ጠላ ጠጥቼ የሰከርኩት አስረኛ ክፍል ሆኜ ግዛው ጌታነህ ጋብዞኝ ነው፡፡ ሌላ የሚያካሂደው ሰው አጥቶ የጋበዘኝ ግዛው ና አጫውተኝ ብሎ ወስዶኝ ነው፡፡ ሁለት ሽክና ጠላ አስክሮኝ ሌላ ዓለም ውስጥ ገባሁ፡፡

ሳሲቶች ስራ ከሌለባቸው ጠዋትና ማታ ፀሐይ እየሞቁ ተሰብስበው ማውራት ልማዳቸው ነው፡፡ ቀንም ቢሆን እቤት ወይም ጥላ ቦታ ሆነው ማውራታቸው የተለመደ ነው፡፡ ዕለቱ ጠላ የተጠመቀበት ከሆነ ወደተጠመቀበት ቤተ ሄደው እየጠጡ ያወጋሉ፡፡ ውርርድ ይወራረዳሉ፡፡ ጨዋታ አዋቂዎች ይጠራራሉ፡፡ ጓደኛሞች ይገባበዛሉ፡፡ ስራ እየሰሩ ማለትም ሴቶቹ ስፌት እየሰፉ፣ እህል እየለቀሙ፣ ምግብ እያዘጋጁ ይጨዋወታሉ፡፡

ትምህርት ቤት ግቢ ወይም ምድርኮሶ ሄደው ስፖርት የሚሰሩ ወይም የእግርኳስና የመረብኳስ ግጥሚያ የሚያዩ አሉ፡፡ ዓመታዊ የትምህርት ቤቶችን ውድድር ማየቱም አስደሳች ነው፡፡ ሩጫ፣ ዝላይ፣ ኳስ አለ፡፡ አዝናኝ ውድድሮችም እንዲሁ፡፡ የሞጃ ህዝብ የሚገናኝበት ነው፡፡ እኛ አንዲት አንድ ብር በነፍስወከፍ የምናዋጣባት የእግርኳስ ክበብ ነበረችን፡፡ አባላችን ጌትሽ ጠብቄ ወደ ሀረር ወይም ሌላ ከተማ ሄዶ ናፍቀነው ደብዳቤ ልኮልን ተሰብስበን ተነቦልናል፡፡

ትልልቅ ሰዎች ሲሰበሰቡ ሁልጊዜ  ወሲብ ተኮር ወሬ የሚያወሩ አሉ፡፡ በቀልድና ጨዋታ አዋቂነታቸው የሚፈለጉ ደማሞች አሉ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ጨማምሩበት፡፡

2023 ጁላይ 5, ረቡዕ

የሳሲት ወጎች ቁ.12 የቤተክርስቲያናችን ድግሶች

 ሁሉም የሳሲትና የልጅነት ወጎቼ ቢስቡኝም ስለ ቤተክርስቲያናችን ስጽፍ ግን ትዝታው በጣም ያይልብኛል፡፡ ያው ትዝታው የሚገንባችሁ አንድ ነገር ካናደዳችሁ ወይም ካስደሰታችሁ ነው፡፡ ጋሽ ሰለሞን ዴሬሳ ለተፈራ ገዳሙ በአሜሪካ በሰጠው ቃለመጠይቅ ላይ ያለው ነገር ትዝ ይለኛል፡፡ ኤደንም ሆስፒታል ልጠይቃት ሄጄ ያለችኝ አይረሳኝም፡፡ ምነው እንደተመራማሪ ምንጭ መጥቀስ አበዛህ እንዳትሉኝ፡፡ የእነርሱን ወደ ኋላ እመለስበታለሁ፡፡

‹‹ምንድነው ስሜታዊ የሚያደርግህ? ሰሞነኛ ነበርክ እንዴ?›› ለሚለኝ ሰው ‹‹አልነበርኩም፤ የሰሞነኛ ልጅ ግን ነበርኩ›› እላለሁ፡፡ በተለይ ትንሽ ልጅ ሆኜ ምናልባትም አምስተኛ ክፍል አካባቢ ድረስ ቤተክርስቲያናችን ለኔ በጣም ቅርበት ሊኖራት የቻለው አባቴ መርጌታ ስለሆነ በበዓላት ወቅት ስሄድ ሁልጊዜ ከሱ ሳልለይ የቤተክርስቲያኗን አገልግሎቶት ስለምካፈልና ትርዒቱን ሁሉ ስለማይ ነው፡፡ ከሁሉም ከሁሉም ድግሳቸው ይምጣብኝ፡፡ ቄሶቹ ድግሳቸውን እያሳዩ ያማልሉኛል፡፡ የቄስ ትምህርት ተምሬ ዲያቆን ወይም ቄስ ሆኜ ዳቦ እንድበላ ይመክሩኛል፡፡ በአንጻሩ ወደ መንግስት ትምህርት አዘነበልኩ፡፡ ይኸው መንግስት የቆረጠልኝን የማያድግ ምንዳ እየተቀበልኩ እኖራለሁ፡፡ ቤተክርስቲያን ትንሽ የሚከብደኝ መቆሙ ነው፡፡ እግራችሁን ያማችኋል፡፡ ባለፈው ወርቅጉር ገብርኤል ከሳሲቱ ከ16 ዓመት በኋላም ሆነ ሳሊተ ምህረት ለዶክተር ፍስሃ ቁርባን ከሃያ ዓመት በኋላ ሳስቀድስ በመምህርነቴ መቆምን ስለለመድኩት ነው መሰለኝ ቅምም አላለችኝ፡፡ አንድ ዘመዴ ደግሞ ይኸውላችሁ ከምሳ ሰዓት እስከ ምሽት ድረስ ለማንቸስተር የዋንጫ ግጥሚያ ሰው በዝቶ ወንበር ሳያገኝ ቀርቶ ቆሞ ነበር፡፡ ይኸውም ቦታ እንዳይያዝ ብሎ ቀድሞ ገብቶ ነው፡፡ ማታ ሲያገኘኝ ››አቤት! ቀን የቆምኩ አሁን አለቀ፡፡ ይሄኔ እኮ ቤተክርስቲያን ቢሆን አንድ አፍታም አልቆምም!›› ያለውም ትዝ አለኝ፡፡ ምሳሌ ሳላበዛ ልመለስ፡፡ ያቺ የኮረብታ ላይ ታቦት ከሩቅ ውበት አላት፡፡ የኖረች ቤተክርስቲያን ነች፡፡ በስተምዕራብ ደጀሰላሙ አለ፡፡ እሱ የቤተክርስቲያኑ ምግብ ቤት ነው፡፡ ሁለት ረጃጅም አግዳሚ ገበታዎች ተሰቅለዋል፡፡ ካህናትና ሌሎች ምዕመናን በረድፍ ተቆምጠው የሚበሉባቸው ናቸው፡፡ ዋንጫዎችም አሉ፤ መስቲና ገንቦም አልረሳሁም፡፡ ‹‹ና፣ አባትህ ጉያ›› እባላለሁ፡፡ መጀመሪያ ዳቦ ይቆረሳል፡፡ መዓዛው የሚያውድ የጥቁር ወይም የነጭ ስንዴ ዳቦ ነው፡፡ ዓይነውርቴም አለ፡፡ እናንተ አነባበሮ ነው የምትሉት፡፡ እንጀራው ይከተላል፡፡ ከታች ቅይጥ ወይም ስንዴ እንጀራ፣ ከላይ ጤፉ ይቀርባል፡፡ ጠላው በዋንጫ ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደተሰየመ ነው፡፡ ደብተራ ዘለቀም አሉ፡፡ መምሬ ከፈለኝም አሉ፡፡ መምሬ ሃብቴም አለ፡፡ የአክስቴ የአበባ የሺ ልጆችን ያሉ መሰለኝ፡፡ አንዳርግ ያን ጊዜ ዳቁኖ ይሆን? አሁን መርጌታ ሳሙኤል ተብሏል፡፡ በዘመድ ተከብቤ ወጋቸውን እሰማለሁ፡፡ አይ ወሬ ማሳመር እቴ! ዳቦዬን አጣጥማለሁ አይሻልም? በጣም የሚናፈቅ የቤተዘመድ ጉባኤ ነው፡፡ ሁሉም ዘመዶቼና ወገኖቼ ናቸው፡፡

ማምየለኝ ማርያም ያለው ሌላው የማዕድ ትዕይንት አባቴ ማህበር ጋ ነው፡፡ የአባቴ ማህበር ቤት አንዱ መቃብር ቤት ነው፡፡ ማህበሩ ከነ ጋሽ ብርቅነህ ተክለወልድ ጋር ነበር፡፡ መቃብር ቤቱ ውስጥ የተቀበሩት ሰዎች የለበሱትን አፈር በባዶ እግራችን እየረገጥን ጥግጥጉን ቁጭ ብለን ዳቦና እንጀራ እንበላለን፡፡ ባለፈው እንደጻፍኩላችሁ ጫማ የለንም፡፡ አፈሩን በባዶ እግራችሁ የመርገጥን ስሜት እስኪ ለአንድ ደቂቃ አስቤት - ወዲያውም ኢሜጀሪ ልስራባችሁ፡፡ ጠላም እንጠጣለን፡፡ ቢራ እንጂ ጠላና አረቄ አያሰክረኝም ብያችኋለሁ፡፡ በብዕረኛው የሞጃ ልጅ ነበር በሌላ ጽሑፍ? ማነህ ባለ ሳምንት የሚለው መዝሙራዊ ጥያቄ ከማህበሩ ሥነሥርዓት በተለይ ትዝ ይለኛል፡፡ በማህበር ቤቱ የቄስ ቡራኬም ግድ ይላል፡፡ ከአባቴ ማህበር ቤት ሌላ ከቤተክርስቲያኑ ግቢ ውጪ የነ አበባ በላይነሽ አለች፡፡ ሌሎችም አሉ፡፡ ትረካው ምልልስ፣ ልብ ሰቀላ ምናምን ስለሌለው ይቅርታ፡፡ ሌላ ቀን ባያሌው እጨምራለሁ፡፡

እሁድ እሁድ ከሆነ ወይም ለፍልሰታ ሁሉም ሰው ቆሎና ዳቦ ያመጣና ያ አንድ ላይ ተደባልቆ እየተቀነሰ ይታደላል፡፡ ጣዕሙ ልዩ ነው፡፡ የእሁዱና የፍልሰታው እንዲሁም ሌላው የሚበላው ቅዳሴ ጠበል ከተጠጣ በኋላ ነው፡፡ ስጽፍ በመጨናነቅ ሳይሆን አንዴ ጽፌ በመላክ ነው፡፡ እንደወረደ ይባላል፡፡ ዋናው ዓላማዬ በጊኒያዊው ደራሲ ካማራ ሌ አምሳል በእንግሊዝኛ መጻፍ ነው፡፡ ያው እሱ በፈረንሳይኛ ቢጽፍም ትርጉሙ እንግሊዝኛ ነው፡፡ ያውም ሙሉ መጽሐፉን አላገኘሁትም - ፍለጋ ላይ ነኝ፡፡ የዩቱቡን ትረካ ቀድሜ ማድመጥ ስላልፈለግሁ ነው፡፡ ሁለት ቅንጫቢ ምዕራፎችን ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መጻሕፍት አግኝቼ ተለከፍኩ፡፡  ቤተክርስቲያናችን ብዬ ርዕስ ብሰጠውም ከቤተክርስቲያኗ ውጪ የሚካሄዱ በዓላትም አሉን፡፡ ከአሁን በፊት ስለ ጥምቀት ስጽፍ ነካክቻቸዋለሁ፡፡ ጥምቀትና አስተርዕዮ ማርያም ታቦት የሚወጣባቸው ናቸው፡፡ ይህም ልዩ ያደርጋቸዋል፡፡ ያኔም ድግስ አለ፡፡ ለጥምቀት ታቦት ባደረበት ሲሆን አለስተርዮ ደግሞ በቤተክርስቲያንና የማርያም ማህበር ባላቸው ዘንድ፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው ወገኖቼ    

ገጣሚ ሰለሞን ደሬሳ በአሜሪካው ቤቱ ለተፈራ ሲያወጋ ‹‹ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ባህል ነበር ያደግሁት›› ያለውና ኤደን ሆስፒታል ሳለች ‹‹እንደ ዱሮው ቤተክርስቲያን ሳሚ ብትሆን ደስ ይልህ ነበር?›› ያለችኝ ትዝ አለኝ፡፡ የሰለሞንን አስተዳደግ እጋራዋለሁ፡፡ ለኤደን ጥያቄ ምላሼ ከእርሷ ምኞት በተቃራኒው ነበር፤ እሷ ቤተክርስቲያን ሳሚ መሆን ባትፈልግም እኔ ግን እፈልጋለሁ፡፡ ጂጂ ናፈቀኝ የኛ ቤት ጨዋታው እንዳለችው ናፈቀኝ የማሪያም ድግስ ልበል እንዴ?

 

የሳሲት ወጎች ቁ. 11 ተናፋቂ የመምህራን አባታዊና እናታዊ ግሳፄ


ከመምህራን ጋር የነበረን ግንኙነት የፈጣሪና የፍጡር ዓይነት ነው ለማለት አይቻል ይሆን? እንደ ፈጣሪ ሁሉ አክብሮታችንን አንነፍጋቸውም። ለአንዳንድ ጠበቅ አድርገው ለሚይዙን መምህራን ወደ አምልኮ የሚቀርብ አካሄድ ነበረው። ፍቅር ግን በልብ የሚያዝ ስለሆነ እንውደድ እንጥላ በልባችን ስለምንይዘው አይታወቅብንም። መምህራን በዚያ ሁኔታ በአንዲት ትንሽ ከተማ እየኖሩ ለእኛ የዕውቀትን ማዕድ ስላቋደሱን እናመሰግናለን። የሥራ ጫናውንና የኖሩበትን ሁኔታ አስታውሼ ያዘንኩላቸው እኔ መምህር ከሆንኩ በኋላ ነበር። መቼም ከስንት ተወዳጅ መምህር በምን ምክንያት እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ የሚጠላችሁ አይጠፋም። እኔና አንድ ሳሲት የተማረ የዕድሜ እኩያዬ መምህር በሳሲት ስለሚጠሉን መምህራን አንስተን ነበር። እሱ የሚጠሉኝ ያላቸው ለኔ ጥሩ ሰው ነበሩ። የሐሳብ አለመስማማት ይሆናል። እኔን የሚጠሉኝና በተቻላቸው አቅም እንደማልችልና እንደማልረባ ይነግሩኝ የነበሩት መምህር ሁኔታ ይደንቀኛል። በአስገራሚ ሁኔታ አንድ ቀን በሆዴ ቂም ይዤ በአጠገባቸው ሳልፍ ጠሩኝ። ጠርተውም ገላመጡኝ። የሰውን ልብ ያያሉ። አሉታዊ ስሜትን ማንበብ ይችላሉ። እርሳቸው ውስጥ ያለውና እኔ ሆድ ውስጥ ያለው ጥላቻ ተጋጨ መሰለኝ። መቼም የማይታረም የለምና ታርመው በአንድ የፌስቡክ ልጥፌ ላይ "ወጣቱ" ብለው የምስጋና ቃል ጽፈውልኝ አገኘሁ። ጓደኛዬን የሚጠሉት መምህር ይሰድቡት ነበር፤ እኔንም የሚጠሉኝ እንደዚያው። እሱን የሚጠሉት ግን እኔን ይወዱኛል። ነክተውኝ አያውቁም። 

የተናፋቂ የመምህራኔን አባታዊና እናታዊ ግሳፄ ላስከትል። ሁለቱ መምህራን ተወዳጅ ናቸው። መጀመሪያ ስለ ሴቷ አስተማሪያችን ልጻፍ። ታች ክፍል አስተምረውኛል። አንድ ቀን እርሳቸውና ሌላ ሴት አስተማሪዬ ገበያ ላይ አገኙኝ። አምስተኛ  ክፍል እሆናለሁ። ጤፍ ተሸከምልን አሉኝ። በደስታ ተሸክሜ ከኋላቸው ተከተልኳቸው። ወሬ ይዘው ስላላዩኝ አቅጣጫ ቀይሬ ጠፋሁባቸው። ያስደነግጣል? አዎ። አልጠፋሁም። አንባቢዬን ትንሽ ላስደንግጥ ብዬ ነው። ተሸክሜ ተከትያቸው ትምህርት ቤት ግቢ ካለው ቤታቸው ደረስን። ጤፉን አውርጄ ልሄድ ስል ቲቸር ጠራችኝ። "ና፣ እንካ" አለችኝ። ሁለት ባለ ሃያ አምስት ሳንቲሞች ነበሩ። ይህ ገንዘብ ያኔ ዳቦና ሻይ ይገዛል። ወይም ትልልቅ ሰዎች እንዳሉኝ ቢቆጠብ ሳድግ ተጠራቅሞ የአንበሴን መኪና የሚመስል ያስገዛኛል። ቲቸር እጇን ዘርግታ  ብትለምነኝ አሻፈረኝ አልኩ። "ተቀበል አንተ!" ብላ ሰትቆጣኝ ግን ልትቀጣኝ መስሎኝ ተቀበልኩ። በመቀበሌ ግን በጣም ተጨነቅሁ። "ሂድ! ደህና ዋል!" ስትለኝ ሄድኩ። ምን እንደገዛሁበት ረሳሁት። ሌላ ቀን ስድስተኛ ክፍል ሆኜ ወንድ መምህራችን እንደወትሮው እንጀራ እንድገዛ ላኩኝ። ገዝቼ መጣሁና ሰጠኋቸው። ምግብ እየሰሩ ነበር። ከዉጪ ቆሜ እጄን ሰደድ አደርጋለሁ እንጂ ወደ ውስጥ አላይምም አልገባምም። ያን ቀን ግን ጠሩኝ። በእጃቸው ቋንጣ ዘረጉልኝ። አልቀበልም አልኩ። "ተቀበል አንተ!" ብለው ተቆጡኝ። ተቀበልኩ። የሁለቱ መምህራን ግሳፄ እናታዊና አባታዊ ነው። በመምህራን መታዘዝ እንደ መመረጥ ይቆጠር ነበር። ተመርጠን ክፍያ መቀበል በጣም ነውር ነበር። ስለዚያም ነበር አይሆንም ማለቴ። ሲገስፁኝ ተቀበልኩ። ትዝታውም አሁንም አለ።

2023 ጁላይ 3, ሰኞ

በእርስበርስ ጦርነት ውስጥ የመኖር ጥበብ - ክፍል 1 - ከጉዞ በፊት መደበኛ ሚዲያን፣ ማህበራዊ ሚዲያንና ማናቸውንም መረጃ መከታተል


ይህን ጽሑፍ የሚያነብ ሰው የእርስበርስ ጦርነት የሚለውን አገላለጽ ለምን ተጠቀምክ ሊለኝ ይችላል፡፡ ስያሜው የሚያጣላን አይመስለኝም፡፡ በመፍረስ ላይ ባለች አገርም ሊሆን ይችላል፡፡ የፌደራል መንግሥትን ሥልጣን ለመቆጣጠር የሚደረጉ ትንቅንቆች የፈጠሩት ሽብርም ሊባል ይችላል፡፡ ውስጣዊ ቅኝግዛትም ተባለ መንግሥታዊ ሽብር፣ ወደ ሥልጣን ለመመለስ የሚደረግ መውተርተርም ተባለ በስንት ስለት የተገኘ ሥልጣንን የማስጠበቅ የውልየለሽ አጥፊ አጀንዳዎች ትርዒት፣  የዘር ማጽዳትም ተባለ በዉጪ ኃይሎች የሚዘወር አለመረጋጋት ለማናቸውም ስያሜውን ለጊዜው ለባለሙያዎች እንተውላቸው፡፡

እዚህ ደረጃ ላይ ለምን ደረስን የሚለውን ሁላችንም በልምድና ዕውቀታችን ልክ ለመመለስ እንሞክር፡፡ እዚህ እሳት ውስጥ ራሳችንን ላለማግኘት ለምን አልሞከርንም የሚለውንስ አስበንበት ይሆን? ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም እንዲሉ አሁን በዚህ ሁኔታ ላይ መውደቃችንን እንጂ ስላለፈው ብዙ መጨነቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ህዝብ ሞቶ፣ ሌሎች ሚሊዮኖች የአገር ውስጥ ስደተኞች ሆነው፣ ከቁጥጥር ዉጪ ሊወጣ የሚታገል የኢኮኖሚ ችግር ነግሦ፣ በየቦታው ሥርዓት አልበኝነት ሰፍኖ፣ ረሃብ ፀንቶ፣ የአጋች ታጋች ድራማዎች በዝተው፣ ኢትዮጵያ የማትመስል አገር ውስጥ እየኖርን፣ ስለነገ ፈጽሞ እርግጠኛነት አጥተን እያልን መቀጠል እንችላለን፡፡ በዓለም ላይ አሉ ከሚባሉት አስጊ ሁኔታዎች ብዙዎቹን እያስተናገደች ባለች አገር ውስጥ እንዴት እንኑር? እስካሁንስ ያለፉትን አምስት ዓመታት እንዴት ኖርን? እነሆ አንዳንድ ነጥቦች፡፡

ሰዎች በተለያዩ ነገሮች ተጠምደዋል፡፡ ነጋዴዎች ሆነው በየዕለቱ በሚንረው የዋጋ ግሽበት ምክንያት ብራቸው ሚሊዮን ገብቶ ሲራባ ልባቸው ጠፍቶ ሌሎች ሚሊዮኖችን ፍለጋ ይቃትታሉ፡፡ ወይም ሁለት ከተሞች ላይ የሚሰሩ ተቀጣሪዎች ሆነው ከአንዱ ወደ ሌላው ከተማ እየተመላለሱ ይኖራሉ፡፡ ባሉበት እንደምንም ሊያሟሉት የሚችሉትን አገልግሎት ለማግኘት ወደ ትልቅ ከተማ ይሄዳሉ፡፡ በአጭሩ በልዩ ልዩ ምክንያቶች ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እስከ ዛሬ በብዙ ሰዎች ዘንድ ያየሁት ክፍተት ቢኖር መጓጓዛቸውን እንጂ የሚጓጓዙበት መንገድ ወይም መዳረሻቸው ሰላም መሆኑን እንደማይከታተሉ ነው፡፡ በእርግጥ ሰላም ባይሆን ሾፌሩ ይነግረን ነበር፣ መንገድ ይዘጋ ነበር፣ እንሰማ ነበር ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይህ ፈጽሞ ስህተት ነው፡፡ በአጋጣሚ ስለ መንገዱና መዳረሻቸው ከሌላ አካል መረጃ ልንሰማ እንችል ይሆናል ከማለት ሌሎችን የማወቂያ መንገዶች ሆነ ብሎ ማጥናትና መፈለግ ግድ ይላል፡፡ ሾፌሩ ያልነገራችሁ እሱ ወደሚሄድበት አቅጣጫ ከሱ ብሄር፣ ከመኪናው ታርጋ፣ ካለው ትውውቅ፣ ከኃይማኖቱ ወይም ከሚናገረው ቋንቋ አንጻር በግሉ ችግር አይገጥመው ሆኖስ ቢሆን? መንገዱ ያልተዘጋው ያን ያህል ለትራፊክ አሳሰቢ ነገር የለም ብለው በወሰኑ የመንገድ ትራንስፖት ሰዎች ወይም አገሩ ሰላም ነው የሚል ስዕል ለመሳል በፈለጉ ፖለቲከኞች ውሳኔ ቢሆንስ? አንዳንዴ መሄድ ችግር የለው ይሆናል፡፡ መምጣት ከባድ ይሆናል፡፡ ለአንዱ ችግር የሌለው ለሌላው ይኖረዋል፡፡ ሚሊዮኖች በሚሞቱበት አገር መቶ ሰዎች ሊሞቱ ወይም የተወሰኑ ሺዎች ሊንገላቱ ይችላሉ ብሎ የሚጠነቀቅላችሁ ያለ ይመስላችኋል? እንዳትታለሉ! እንሰማ ነበር የሚለውም አይሰራም፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አይገመቴ ሁኔታዎች የመፈጠር ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ ሾፌሩም አይነግራችሁም፣ መንገዱም አይዘጋም፣ ልትሰሙ የምትችሉበትም ዕድል የለም፡፡ ‹‹ታዲያ ምን ተሻለን?›› ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ገና ለገና ችግር ሊመጣ ይችላል ብሎ አስጨነቀን ብላችሁኝም ይሆናል፡፡ ግድ የላችሁም፡፡ ትንሽ ሃሳብ እናፍልቅ፤ ካለፉትም ጊዜያት እንማር፡፡ የሚፈጠሩት ችግሮች በአመዛኙ በፖለቲካ ውሳኔ የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ አንድ ቡድን ወይም አካል አንድን ግብ ለመምታት ሲል የሚያደርጋቸው ናቸው፡፡ እንጂ ተራ የእንትን ብሔር ወይም ኃይማኖት አባል ተበድዬ፣ ምን ብዬ ብሎ አይነሳም፤ አይነካችሁምም፡፡ ግለሰቦች በራሳቸው ተነሳሽነት የሚወስዷቸው እርምጃዎች በጣም ውሱን ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ቡድኖች የሚያንቀሳቅሷቸውን ርዕሰጉዳዮች መከታተልና የአካሄዳቸውን አዝማሚያ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡ መረጃዎቹ ከየት ይገኛሉ ከተባለ ከመደበኛ ሚዲያዎች፣ ከማህበራዊ ሚዲያዎችና ከሌሎች ምንጮች ይሆናል፡፡ የአገሪቱን ፖለቲካ አካሄድ በንቃት መከታተል ሕይወትን የሚታደግ ውሳኔ ላይ ሊያደርስዎት ይችላል፡፡ ፖለቲካውን እንኳን ባይከታተሉ መደበኛ ዜና ይከታተሉ፡፡ መደበኛ ሚዲያዎች ጭራሽ የማይዘግቧቸው ወይም ዘግይተው ምናልባትም አዛብተው የሚዘግቧቸው መረጃዎች አሉ፡፡ ቴሌቪዥን አይቼ፣ ሬዲዮ ሰምቼ፣ የእንትን ሚዲያን አካውንት ሰብስክራይብ አድርጌ ዩቱብ ላይ ሰምቼ አይሰራም፡፡ መደበኛ ሚዲያዎች መረጃዎቹን አጣርተው፣ አለቆቻቸውን አስፈቅደው፣ ግራ ቀኙን አይተው፣ ወሬውን እስኪለቁት ብዙ ውድመቶች የመጡባቸውን ጊዜያት አስቡ፡፡ መረጃ እንዲዳፈንም ይደረጋል፡፡ መረጃ ተዛብቶ ይደርሳችኋል፡፡ ወይም ይዘገያል፡፡ ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ስንመጣ ታማኝ የሚሏቸውን ዘጋቢዎች ይለዩ፡፡ እነርሱም ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ አውቀው የሆነ ዓላማ ለማሳካት፣ ብዙ ተከታይ ለማግኘት፣ ሰበር ዜና ለማውጣት ወይም የመረጃ ምንጭ አሳስቷቸው፣ ምናልባትም ከሁለት ወገን ሳያጣሩ ዘግበው ሊሆን ይችላል፡፡ መረጃዎችን ማን ለቀቃቸው የሚለው ወሳኝ ነው፡፡ ያንን መረጃ ከየት አመጣው የሚለውም እንዲሁ፡፡ ግነትም ካለ ልብ ይበሉ፡፡ ስለዚህ የማህበራዊ ሚዲያን መረጃ በሚገባ ማጣራት ያሻል፡፡ በፌስቡክ ገጽዎ የመጡልዎትን ወይም እርስዎ ላይክ ካደረጓቸው ገጾችና አካውንቶች ገብተው ያዩትን ብቻ አይጠቀሙ፡፡ ፈልግ የሚለውን ተጠቅመው ይፈልጉ፡፡ ፍለጋዎትን መረጃው በተለቀቀበት ጊዜ፣ ቦታ፣ ምንጭ መሰረት ማጥራት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ከደብረብርሃን ወደ አዲስ አበባ የሚሄዱ ከሆነ በከተሞቹ ስም፣ በብሔሮች፣ በፓርቲዎች፣ በኃይማኖቶች ወዘተ የዕለቱን መረጃ ሊፈልጉ ይችላሉ፡፡ የፌስቡኩ ለትዊተርም፣ ከቲክቶክም ይሰራል፡፡ ማህበራዊ ሚዲያን በዚህ መልኩ ከተጠቀሙ ወደሚያውቋቸው ሰዎች መረጃ ፍለጋ መደወል ሊኖርብዎት ይችላል፡፡ ከሚዲያ ሚዲያ፣ ከአካውንት አካውንት፣ ከግለሰብ ግለሰብ የወሰዱትን መረጃ ማማሳከርና በውሳኔ ግብዓትነት መጠቀም እንጂ ሌሎች ሰላም ነው ብለው በወሰኑት ውሳኔ ተመስርተው ሕይወትዎንና የሚወዷቸውን ሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ አይጣሉ፡፡ ዘዴ ይፈልጉ፡፡ የመስሪያ ቤት መታወቂያ ያሳያሉ ወይስ የቀበሌ፣ በግልዎ መኪና ይሄዳሉ በህዝብ ትራንስፖርት፣ በሚኒባስ ወይስ በአውቶቡስ፣ ቢጠየቁ ሙያዎትንና ስራዎትን ይደብቃሉ ወይስ ግልጹን ይናገራሉ? መታወቂያው ላይ ስሙ የፊደል ግድፈት እንዳለው ላስቆሙት አካላት በመንገር ራሱን የሌላ ኃይማኖት አባል በማስመሰል  ሸወዶ እንዳለፈው ወዳጄ ሕይወትዎን ያተርፋሉ? ከመንገዱ በኋላስ? የሚያርፉበት ከተማ ሰላም ነው? እስከመቼ? ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ እንወያይበት፡፡

ግለ-ታሪክ

የሁለተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ መዝሙር በመዘመር ሰኔ 30 ተሸልሜ ነበር። ከሁሉም ልጅ በላይ ጮክ ብሎ መዘመርን ማን መክሮኝ እንዳደረኩት አላስታውስም። እንግዲህ አንዱ ሲዘመር ጮክ ተብሎ ነው ብሎኝ እውነት አድርጌው ይሆናል። ብቻ አላውቅም። 8 ክፍሎች በእኔ ምክንያት ብዙ ቀን ተገርፈዋል። "ጉርምስና ነው የማትዘምሩት! ይህ ትንሽ ልጅ ሲዘምር!" እየተባሉ። ከሁሉም ትንሹ ሳልሆን አልቀርም። ሁሉም ሰው ተረት ንገረን እያለ ይይዘኛል። ያን ሳስታውሰው አሁን ሥነጽሑፍ ማጥናቴ ይገርመኛል። አንድ ቀን ማለዳ እናቴ ክፉኛ ደበደበችኝ። በፍልጥ ሳይሆን አይቀርም። ስጋዬ ሳይቦጫጨቅ አንቀርም። ጎረቤታችን ጋሽ ሞገስ ነው ሮጦ መጥቶ የገላገለኝ። እንደምንም ደብተሮቼን ይዤ ወደ /ቤት እያለቀስኩ አመለጥኩ። ያስደበደበኝ ቁርስ መጠየቄ ነው። ቸግሯት አይደለም። ሙሉ ተመን ያላት ገበሬ ነች። ምግብ ያለመስራት ስንፍና ነው። ትምህርት ቤት ገብቼም ለቅሶዬ አላቆመም። ስዘምርም ጮክ ብዬ እያለቀስኩ። ቲቸር በመዝሙር መሐል ቀጥ ብለው ከቆሙበት መጥተው "መዘምር ተወው" አሉኝ። ጎረቤታችን የነበረን ልጅ /ብርሃን አግኝቼው "አቤት እናታችሁን ስትፈሯት!" አለኝ። ወንድሜ በዓመቱ በአደጋ ሞተ። ልጄን ቀጥቅጬ ገደልኩ አለች። አደራ በትዳራችሁ ስትናደዱ በልጆች ላይ እንዳትበቀሉ።

2023 ጁላይ 2, እሑድ

የሳሲት ወጎች ቁ. 10 ሰዎች ራሳቸውን ያጠፉባቸው መንገዶች

 የሳሲት ወጎች 

ቁ. 10

ሰዎች ራሳቸውን ያጠፉባቸው መንገዶች


ወቅቱ ክረምት ነው። በባዶ እግርህ በጭቃ ላይ እየሄድክ በጎች ስታግድ ውለሃል። ያቺ አመለኛ በግ የሰው ስንዴ በልታ በጅራፍ እንዳታስገርፍህ አእምሮህ ቀኑን ሙሉ ነቅቶ ውሏል።

አንተ በጨዋታ ተመስጠህ በጎችህ እሰው ማሳ ቢገቡ ልጆች ከየአቅጣጫው ይዘፍኑብሃል እንጂ ቀድመው አያስጠነቅቁህም።

"አብላው ብቻ

አንት ግትቻ

አብላው ባቦ 

አንት ወታቦ

አብላው ብዬ

አንት ወርዬ"

ይህ የልጆች ዘፈን ባለ ማሳውን ለመጥሪያ የሚያገለግል ደወል ነው። ያኔውኑ አይመታህም። ተደብቆ መጥቶ ሳታስበው ይዞ እግሮችህ የጅራፍ ምልክት እስኪያወጡ ይገርፍሃል። ትንሽ ኢየሱስ ትሆናለህ። እሱም ትንሽ አይሁድ። የእግርህ ጣቶች መሐላቸው በክረምቱ ዉኃ ርሶ ሲሰነጠቅ ያምሃል። ጠዋት የበላህ ነህ። ማታ ገብተህ እንጎቻ ከደረሰ ወይም ቆሎ ካለ እንደሚሰጡህ ታስባለህ። ያለዚያ ማታ ምግብ ሲዘጋጅ ከቤተሰብህ ጋር ምድጃ ከበህ እሳት እየሞቅህ ስትጠብቅ አልደርስ ብሎህ እንቅልፍ ያዳፋሃል። ስለ ልጅ አስተዳደግ በክፍል ዘጠኝ ስለጻፍኩ ያንን ብታነበው ጥሩ ዳራ ይኖርሃል። የዚህን ጽሑፍ የእንግሊዝኛ ትርጉም እያነበብክ ከሆነም የኢትዮጵያን ሕይወት ስትረዳ ከሌላ ፕላኔት የመጣ ታሪክ የምታነብ ይመስልሃል። ይህን የስድስት ዓመት ልጅ ተደጋጋሚ የዕለት ውሎ በአንድ ሰቅጣጭ የምሽት ገጠመኝ ልጨርሰው። ራት ልንበላ ስንጠባበቅ የጥይት ድምፅ ሰማን። ከጎረቤታችን ያለው ፖሊስ ጣቢያውና እስር ቤቱ ስለሆነ ከዚያ መስሎናል። አይደለም። መረጃው ወዲያውኑ ደረሰን። ደግ ጎረቤታችን ነበር። ከረሜላ ይሰጠናል። ይወደናል። ከሰንደል መያዣው ወረቀት ጫፍ ያለችውን ሳንቲም የምትመስል ብረት አውጥተን "ጋሼ መክብብ፣ ከረሜላ ስጠን" ስንለው እንደሚሰጠን እንደ ጋሼ መክብብ ያለ ደግ ጎረቤታችን ጋሼ ተጌ ነው ራሱን ያጠፋው። ምክንያቱን አላውቅም። ራሱን ያጠፋው ጥይት ጠጥቶ ነው አሉ። 

በትንሽ ተልካሻ ምክንያት ወይም በአንድ መቶ ብር ዕዳ፣ በአራጣ ብድር፣ በብስጭት ራሳቸውን በገመድ አንቀው የሚገድሉ አሉ። ወንዝ የሚገቡ አሉ። 

ወያኔዎች በአገሩ ሰው እየተመሩ አንዱን አሳደዱት። ሽፍታ ነህ ብለው ሰላም ነሱት። በርከት ባለ ሰራዊት ሲሳደድ በባሶና ወራናና በሞጃና ወደራ ድንበር ሊደርሱበት ሆነ። የሚደርስለት የለም። ሁሉም አቀርቅሯል። ተስፋ ቆርጧል። ወይም አይተባበርም። እንዲያውም ሰዉን ለማስጠቃት ጠመንጃ አለው ብሎ ይጠቁማል። ያ የተሳደደ ሰወሰ ራሱን አጠፋ። ከያዘው ጠመንጃ ጥይት እንዳይጠጣ አልቆበት ሊሆን ይችላል። ራሱን ያጠፋው በጩቤ ሆዱን በመቅደድ ነበር። ስቃዩን ለማሰብም ይከብዳል። 

የአይጥ መርዝ ጠጥተው ቶሎ ቤተሰብ ደርሶላቸው አመድ ወይም ወተት ተግተው የዳኑ አሉ። የሞቱም እንዲሁ። 

ዝርዝሩ ብዙ ነው። 



የሳሲት ወጎች ቁ. 9 የልጆች አስተዳደግ

የሳሲት ወጎች
ቁ. 9
የልጆች አስተዳደግ

ልጅ መውለድ ቀላል ነገር አይደለም። በተለይ እንደ ሳሲት ባለው ቦታ ማርገዝ ራሱ አስቸጋሪ ነው። አንዲት እናት ቆላ ውስጥ አረም ስታርም ውላ ማታ ደጋ ወዳለው ቤቷ ወጥታ ራት ሰርታ ልጆቿንና ባሏን ካበላች በኋላ እሳት ስትሞቅ ምጥ መጣሁ ይላታል። የጎረቤት አዋላጆች ተጠርተው ያዋልዷታል። አርግዞ ከባድ ስራ መስራት ብቻ ሳይሆን በምትወልድ ጊዜ የምትበላውን ነገር ለማዘጋጀት አቅሙ የሌላት ብዙ እናት ነች። ቢያንስ ሁለት እናቶች ይህን መራራ ሐቅ ሲያወጉ ሰምቻለሁ። የወሊድ መቆጣጠሪያ ስለማይታወቅ ራስ በራስ መውለድ ነው። በወሊድ ጊዜ እስከ ሞት የሚያደርስ ሁኔታ ቢከተል ደረጃውን የጠበቀ ህክምና ስለሌለ ከመሞት ዉጪ ምርጫ የለም። እንደምንም የተወለደው ልጅ በዕድሉ ያድጋል ይባላል። ዕድሉ ያመጣለትን እያየና እየቀመሰ ያለዕቅድ የሚያድገው ልጅ ዕጣፈንታ በወላጆቹና በመንደሩ የአስተሳሰብ ልክ ይወሰናል። አንዳንዶቹ ወላጆች ለእነርሱ ጥሩ ምግብ እየሰሩ ለልጆች አልባሌ ነገር እንደሚያበሉና ማታ የሚያወጉባት የብቻ እልፍኝ እንዳላቸው እናውቃለን። ባናይም በግና ከብት ስናግድ ልጆቻቸው ነግረውናል። ከስንት አንድ ለልጆቻቸው ፍቅር የሚያሳዩና በደህና የሚያበሉ እንዳሉት ሁሉ 1977ን በቤታቸው ያነገሱ ከንቱ ገልቱዎች አይጠፉም። ደግሞ አለ አንዳንዱ በወጣ በገባ ቁጥር ጉልበቱን በልጆቹ ላይ የሚያሳይ። ሰላምታው ሁሉ ዱላ የሆነ። ልጅ የሚገርፉበትን ምክንያት ስትጠይቋቸው አያውቁትም። መጥፎ ባህሪዎቻቸውን ሁሉ ከወላጆቻቸው ኮርጀው የነሱ ቅጂ በመሆን ጭካኔን በዘር ሐረጋቸው ያስተላልፋሉ። በእርግጥ ከስንት አንድ ልጅን የማይቆጡም ሆነ የማይመቱ ይኖራሉ። ወደ ማሞላቀቅ ደረጃም የሚያደርሱ አይተናል። ይህን ያህል ሳይሆን መጠነኛ ቢሆን ጥሩ ይመስለኛል። ልጅ እንዴት ማደግ እንደሚኖርበት ብዙም አስቤበት ባላውቅም የአሁኑን ዘመን የከተማ የልጅ አስተዳደግ ሳይ አንዳንዴ የሳሲቱን አስተዳደግ መካከለኛ የሆነ ቁጥጥር ቢሆን ልቀበለው ይዳዳኛል። 
ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ አሉ። ይህን የማስተማር ነገር ግን ልጆችን በመለያየት ሲሆን አልደግፈውም። ባለፈው በዚህ ጥፋት በትዋተር ልጥፌ ክፉኛ የወቀስኳቸው የሳሲት ሰው አሉ። ምናልባት ሰማይ ቤት ቅጣት ካለ ብድሩን ሊያገኙት ይችላሉ። እንጂ ልጁማ አላስተማሩኝ ብሎ አይደባደብ! የተማሩት የት ደረሱ እያለ ይጽናናል እንጂ። በወሬ መሐል ደግሞ የኃይማኖት ቦታም ጠንቋይ ቤትም የሚሄዱ ሰዎች ነገር ትዝ እያለኝ ጻፍ ጻፍ ይለኛል። ምናገባኝ ቆይ! ግማሾቹ ልጅ ማስተማር ማለት ልጅን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ብቻ ይመስላቸዋል። ያው ስላልተማሩ ይመስለኛል ይህ የሆነው። ለዚያውም ልጁ ትምህርት ቤት ሲቀመጥ የሚባክነው ጉልበቱ ያሳስባቸዋል። ሁሉንም የሳሲት ወላጆች ለማድነቅ የምፈልግበት ጉዳይ በመስከረም ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን ሲያስመዘግቡ መምህራን በደንብ እእነዲቀጡላቸው የሚሰጡት ነፃነት ነው። ልጆቻቸውን 
የሚሳደቡ ወላጆች አሉ። በዚያው ልክ የሚያበረታቱም አሉ። የእኔ እናት ከሚያበረታቱት ውስጥ ነች። እንግዳ በመጣ ቁጥር ና ጋዜጣውን አንብብላቸው እያለች የአነባበብ ዘይቤዬን ታደንቃለች። ይህ ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ ነው። ስንተኛ ክፍል እንደሆንኩ ሲጠይቋት ፈጽሞ ያለሁበትን ክፍል ተናግራ አታውቅም፤ ቀጣዩን እንጂ። ለምሳሌ አምስተኛ ሆኜ ቢጠይቋት "ወደፊት ስድስተኛ ነው" ትላለች። በወላጆች በዓል ጥበባዊ ነገር ካቀረብኩ ከዓመት በላይ በአድናቆት ታወራዋለች። ማንበብና መጻፍ መቻሏን በቅርቡ ስፈትናት ትችላለች። የሆነ ነገር ጻፊ ብዬ ስሰጣት የጻፈችው ነገር በእጅጉ ስላበረታታኝ አሁንም አልበሜ ውስጥ አስቀምጬ እየተበረታታሁበት እገኛለሁ። "መዘምር ጎበዝ ነው" የሚል ነው የጻፈችልኝ። ዱላዋ አይምጣብኝ! አሁንም አጥንቴ ድረስ ይሰማኛል!

2023 ጁላይ 1, ቅዳሜ

የሳሲት ወጎች ቁ. 8 ኋላቀርነት ይሰማናል?

 የሳሲት ወጎች

ቁ. 8

ኋላቀርነት ይሰማናል?


ባለፈው ሳምንት ሳሲት እንደሄድኩ ኋላቀርነታችን በደንብ ተሰምቶኛል። አእምሮቸውን ተጠቅመው የበለፀጉ ህዝቦችን በቴሌቪዥን፣ በኢንተርኔትና በመጽሐፍ ስለማውቅ ከእነርሱ ጋር የኛን እንደተፈጠርን ብዙም ሳናስብ መሞት የምገነዘበው ሳሲት ስሄድ ነው። ከሳሲት ወጥታችሁ ገጠር ያለውን ገበሬ ስታስቡት የበለጠ ይሰማችኋል። በዓለም ላይ እየተከናወነ ስላለው ነገር ምን ያህል ያውቅ ይሆን? "አዲስ የመጣችው ጠንቋይ ወፍ አርግፍ ነች። ታውቃለች።" ብለው ሲከራከሩኝ ነገር ዓለሙን ትቼ ተስፋ እቆርጣለሁ።

የሥልጣኔን ነገር ወደኋላ ሄድ ብለን እንየው። የዛሬ ሰላሳ ዓመት የነበረውን ሕይወት አስታውሱ። ደርግ ወጥቶ ወያኔ የገባበትን አካባቢ ማለቴ ነው። ያ አስከፊ ጦርነት ታልፎ አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም እስሮች፣ እንግልቶችና አልፎ አልፎ ፖለቲካዊ ግድያዎች ነበሩ። ሕይወት በዚያን ጊዜ ሽግግር ላይ የነበረች ይመስለኛል። የኢትዮጵያ መንግሥታት በተቻላቸው አቅም አገሪቱን ከዓለም ነጥለው በኋላቀርነት እንደሚያኖሩ ከአሁን በፊት ጽፌያለሁ። ዘመናዊ ነገርና ምቾት ለገዢዎች እና ለእነሱ የቅርብ ሰዎች የተተወ ነው። የኢህአዴግ ዘመን ደርግ ያላስተዋወቃቸውን ነገሮች በሰፊው ያስተዋወቀ ቢሆንም እሱም ከትችት አያመልጥም። ዘመናዊነቱን በአንድ ዘመነመንግሥት ውስጥ ብቻ እንየው። በወያኔ ጊዜ የመጣው ዘመናዊነት ወይም በርን ለዉጪ መክፈት ከከተማ ወደ ገጠር ይለያያል። ገጠር ከፋብሪካ ምርቶች ፌስታልን እንኳን ያየው ስንት ቆይቶ ነው። አንዲት የዕቃ ማሸጊያ ላስቲክ ብትገኝ እሷን በስንት ጥንቃቄ ይጠቀማል። ማናቸውም የፋብሪካ ውጤት አንድ ስራ አይታጣለትም። የፋብሪካ ምርት እንደ ኒውጊኒ ህዝብ ወደ ኃይማኖታዊ አምልኮ በተጠጋ ደረጃ እንክብካቤ ይደረግለታል። ልብሳችን ከቁምጣ ወደ ሱሪ ለመግባት ዘመናትን ወስዶብናል። ሴቶቹ ያለ ክንብንብ አይወጡም። ጫማ አይታወቅም። የአፈር ማዳበሪያ በስፋት የተዋወቀው ዘግይቶ ነው። አንድ መኪና በሳምንት አንድ ቀን ይመጣል። የመንግስት ተቋማት አንድ ትምህርት ቤት፣ አንድ ሐኪም ቤት፣ አንድ ፖሊስ (ጣቢያ አላልኩም)፣ ግብርና ጣቢያ አሉ። የሥልጣኔ በሮቻችን ናቸው። ከከተሜዎች ጋር ለመተዋወቅ ዕድል ይሰጡናል። በእርግጥ መጠጥ ቤቶች አሉ። ሁለት ግለሰቦችም ቤርጎ አላቸው። "ማን ሊያድርበት!" አሉ? ለአዳሪው ችግር የለም። ወፋ ነገሠ ጋ የምትመጡ ከተሜዎች አላችሁ። የአገራችንን ከሥልጣኔ ወደ ኋላ መቅረት በሦስት መንገዶች ላሳያችሁ። አንደኛው የትኛውንም የኢትዮጵያ ክፍል የዛሬ ሰላሳ ወይም ሃያ ዓመት ወደኋላ የነበረበትን አስቡና አሁን ያለውን ለውጥ እዩ። ሁለተኛ አንድን ትልቅ ከተማ ከገጠር ጋር አስተያዩ። ከከተማ ሄዳችሁ እዚያ ገጠር ሦስት ቀን ብታድሩስ? ሦስተኛ ከዓለም ብንነጠልና ለሁለት ዓመት ግንኙነታችን ቢቋረጥ ብላችሁ አስቡት። ኋላቀርነታችን ያኔ ይገባችኋል። አእምሯችንን አለመጠቀማችን፣ በማያስቡ ሰዎች መመራታችን፣ ጣሊያን ሦስተኛ ጊዜ ቢመጣብን የምንሆነውን አለማወቃችን ወዘተ ይታሰበኛል። አንድ ከኒውዮርክ የመጣ ሰው እኔን ደብረብርሃን አይቶና የኑሮዬን ደረጃ ተረድቶ ምን ያውቃል እንደሚለኝ እገምታለሁ። ከበለፀገ አገር ወደ ደሃው ወይም ከከተማ ወደ ገጠር ስትሄዱ ያለው የሥልጣኔ ክፍተት ይገባችኋል። በእርግጥ የትም ሆናችሁ የት ለመሰልጠንና ላለመሰልጠን ቦታና ጊዜ ዋስትና አይሆንም። በቁሳቁስ፣ በዕውቀት፣ ሰውነትን በመጠበቅ፣ በመንፈሳዊ ዝንባሌ፣ ለሰው ባለን አክብሮትና በቴክኖሎጂ የምንኖርበትን ሁኔታ ግላዊ ዝንባሌ እንጂ ቦታ ላይወስነው ይችላል። ለማንኛውም "የሰው የለው ሞኝ"ን ጋብዤ ልሰናበት።


የሳሲት ወጎች ቁ. 7 ከዝዋይ ሁለት የሰው ጥርስ የመጣ ቀን

 የሳሲት ወጎች 

ቁ. 7

ከዝዋይ ሁለት የሰው ጥርስ የመጣ ቀን


አንድ ቀን አንድ በሳሲት አቅራቢያ የሚኖር ታገስ የሚባል ሰው ሸዋሮቢት ጠመንጃ ለመግዛት ወርዶ ወባ ይይዘዋል። በዚያውም ምክንያት ሕመሙ ይጠናበትና ሊሞት ይሆናል። እንዳገራችን ደንብ ለኑዛዜ ንስሃ አባቱ ይጠራሉ። ለንስሃ አባቱም የሰራውን ይናዘዛል። 

"ቦጌን ያስገደልኩት እኔ ነኝ።"

ሰው ሁሉ ተደናገጠ። 

"ምን አድርጎት ይሆን? ጠይቁት እስኪ።" ተባለ። ሰውዬው መቼም መሞቱ ስለሆነ ምንም አይፈራም። ስለዚህ የሚደብቀው የለውም።

"አንድ ቀን ... እእእ ..." 

ሳይናገር እንዳይሞት ፈርተዋል። 

"ለምን አስገደልከው?" አሉ ቄሱ።

መናገር ጀመረ በጣር ድምፅ "አንድ ቀን ምሽት እኩሽና እያለን ዉሻችን ያለ ወትሮው በጣም ጮኸ።" 

"እሺ" 

"እኔም ነገር አለ ብዬ ወደ እልፍኝ መሄጄን ትቼ ቤተሰቡ በሙሉ እኩሽና አደረ።" 

"አቤት!" 

"ባለቤቴ ጠዋት ቀድማ ወጣችና አየች። ተደናግጣ ጠራችኝ።"

"ምን አስደነገጣት?" አሉ እናቱ በልጃቸው ጣር እያለቃቀሱ። 

"እደጅ ሰው አድፍጦ አድሮ ኖሮ ምልክቱ ተገኝቶ።"

"ዕቃ ጥሎ ነው?" 

"አይ፣ ካፊያ አካፍቶ ኖሮ እሱ ያደፈጠባት ዝናብ ሳይመታት ተገኘች። ያቺን ምልክት አይቼ ካፊያው የበጋ ካፊያ ስለነበር ሰውዬው ወደ ቤቱ ሲሄድ የረገጠው አፈር ምልክቱ አለ።" 

"በጄ!" አሉት።

"ያንን ምልክት ተከትዬ ስሄድ እቦጌ ቤት አደረሰኝ።" 

"በወሰን የተጣላችሁ ጊዜ ነው?" አሉት አባቱ።

"አዋድ ...እእእ አቤት.." አቃሰተ። 

"እኔም ጠመንጃ ይዤ ነበር የሄድኩት። ምንም ሳልል ሳልታይ ተመለስኩ። ሳልገድለው የተክለጊዮርጊስን ዓይን አጥፍቶ ታገር ተነቀለ።" 

"አዋ... ሄዷል።" አለች ሚስቱ።

"በስንት ጥየቃ ዝዋይ መሆኑን ሰምቼ ያን ቀን ሊገለኝ አልነበረም! ብዬ የሚገድልልኝ ወዳጅ አገኘሁ። ገዝቼ አስገደልኩት።"

"አቤት አቤት" አሉ ሁሉም። 

"ለገደለልኝን ሰው ገንዘብ እምሰጠው ሰለባ ይዞ ከመጣ መሆኑን ነግሬው ነበር። ያው ቦጌ ገጣጣ ስለሆነ ጥርሱ ያስታውቃል። ሁለት የፊት ጥርሱን አመጣልኝ።"

ቄሱ ፈገግ አሉ። 

"ቦጌንማ ሁለት የፊት ጥርሱን ወርቅ አስተክሎ፣ ወፍሮ፣ ሀብታም ሆኖ ደብረሊባኖስ አግኝቼዋለሁ።" አሉት። 

ሁሉም ሰው ተደናገጠ። 

"ማንን ነው ግደልልኝ ያልከው?" 

"ሃይለማርያምን ነው።" 

"ዋናውን አጭበርባሪ! ወይ ጆሮውን ቢሆን ይታመን ነበር" አሉት።

እሱም ደንግጦ ፍጥጥ አለ። ተመልሶ ተኛ። ሳይሞትም ቀረ። ሐኪም ቤት ወስደው አሳክመውት ዳነ። 

በሌላ ጊዜ ሃይለማርያም ሰክሮ አወራ እንደተባለው ቦጌን በጨለማ በሰከረበት ደብድቦ ሲወድቅለት ጥርሶቹን በፔንሳ አውጥቶ ሳሲት በማምጣት አንድ ሺህ ብር ወስዷል። ሳሲት ሌላ የበቀል ጣጣ ይጠብቃታል።

የሳሲት ወጎች ቁ. 6 የሳሲት ማስተር ፕላን

 የሳሲት ወጎች

ቁ. 6

የሳሲት ማስተር ፕላን


ማስተር ፕላን ሲባል የምታስቡትን ለመገመት አልቸገርም። ፈረንሳዮች ለአንዲት ከተማቸው ዲዛይን ሰርተው ያንን እንዴት ወደ መሬት እንዳወረዱ እያሰባችሁ ይሆናል። ምክንያቱም እንደ አንድ ወዳጄ 'ሳሲት' ከድምፀቷ የፈረንሳይ ከተማ መስላችሁ ይሆናል። ወዴት ወዴት! ኑ ወዲህ። ተጉለት ነን። በመሐል ተጉለት ተሰይመናል። በጊዜ መርከባችን ወደ 1980ዎቹ እንቅዘፍና ከሳሲቱ ፒያሳ ማለትም ከጋሽ ኪዳኔ ጨርቆስ ደጅ እንገኝ። ወደ ኋላ መሄዱ ብዙም እንደማያዞራችሁ በመተማመን በጋሽ ኪዳኔ ወይም በመቶአለቃ ጠጅ ቤት እንሰየም። ረጅሙ ጠጅ ቤት የፖሊሶች፣ የአስተዳዳሪዎች፣ የባለመኪኖች፣ የወፋ ሂያጆች፣ የእንግዶች ሁሉ መናኸሪያ ነው። በእርግጥ መናኸሪያ የሚባል መኪና ማቆሚያ ባይኖርም መኪና የሚቆመው ከዳጃቸው ነው። ወያኔ የታዋቂውንና የተፈሪውን የተጉለቱን ሽፍታ የአየለ ዝቄን መሞትና መቀበር ስትሰማ ማመን አቅቷት ከመቃብር አውጥታችሁ ደብረብርሃን አምጡልኝ ባለች ጊዜ አስከሬኑ ከመቃብር ወጥቶ በመኪና የተጫነው እርሳቸው ደጅ ነው። ሌላ ሽፍታም በዘመቻ ተገድሎ የአስከሬኑ ፊት ተገልጦ ለህዝብ ማስተማሪያ በድንክ አልጋ የተቀመጠው እርሳቸው ደጅ ነበር። ይቅርታ! የምናወራው ስለ ማስተር ፕላን ሆኖ ስለማስተር ግድያ ጣልቃ ወሬ አስገባሁ። ከጋሽ ኪዳኔ ቤት ፊት ለፊት አራት ሰርቪስ ክፍሎች ያሉት የነ ዓለምሸት አራት ባራት አለ። ከሱ ጀርባ የኛ ፎቅ ተሰይሟል። ከኛ ቤት ቀጥሎ ዋናው ጠመንጃ አላቸው ተብሎ የተጠቆመባቸው ሰዎች መግረፊያ የዱሮ ሕብረት ሱቅ አለ። ወያኔ ሲገባ የታጋዮች ካምፕ ነበር። በኋላ ደግሞ እንደ አስተዳደር ማዕከልም እንደ ፖሊስ ጣቢያም አለገልግሏል። ከሱና ከእኛ ቤት ፊት ለፊት ገበያው ይገኛል። ከዚያ የጋሽ ጌታነህ ኮረብታ ሱቅ አለ። ከሱቁ ጎን የልጃቸው የግዛው ዳቦ ቤት አለ። ለ1987 ዓ.ም. ምርጫ ህዝቡ ጎረቤታችን በሆነው ህብረት ሱቅ ደጅ በተሰበሰበበት ቀስቃሹን ለምኜ በድምፅ ማጉያ ለመናገር ፈልጌ ነበር። 

"ከፎከርክ ነው!" አለኝ። 

"እሺ" ብዬ ተስማማሁ። ፎከርኩ። ሕዝቡ በሙሉ አንድ ብር አውጥቶ ያውለበልባል። ያንን ሁሉ ብር ለመሰብሰብ ፈራሁ። የክርስትና አባቴን የጋሼ አስራተንና የአያቴን የዘነበን ወሰድኩ። ልጆች ከበቡኝ። ምን እንደማደርግበትም ሐሳብ አመጡ። በአንዱ ብሩ ሦስት ዳቦና አንድ ሻይ በላሁ፤ ጠጣሁ። የግዛው ዳቦ ቤት ከቤታችን ፊት ለፊት ተሰርቶ ጭስ ማውጫው ከፍ ብሎ የተሰራ ነበር። የዳቦው ሽታ ጠዋት ማታ ሆዳችንን ያላውሰዋል።  የሳሲት ቤቶች ታዋቂው ግሪካዊ የታሪክ ፀሐፊና ተጓዥ ሄሮዶተስ እንደፃፈው ከአንዱ ቀጥሎ ሌላው፣ ከአንዱ ቀጥሎ ሌላው የተጣበቁ ናቸው። ሄሮዶተስ የፃፈው ስለ አገሮች ነው። እያንዳንዱ ግዛት ስለ ራሱ እንጂ ከእርሱ ጎን ያለውን ያለማወቅ ችግር አለበት ይለናል።  ከአንዱ ቤት ቀጥሎ ያለምንም ፋታ ሌላው ቤት ተለጥፎ ተሰርቷል። ግድግዳ ስለሚጋሩ ቤት አፍርሶ መስራት አይታሰብም። ክረምት በመጣ ቁጥር በጎርፍ ፍሳሽ ይጣላሉ። ጮክ ብለው ካወሩ ወሬያቸው ይሰማል። እንደ ሱማሌ አንዱ ወደ ሌላው ቤት ዘው ብሎ አይገባም። ምንም ሳይጠያየቁ ዓመታት ሊያልፉ ይችላሉ። ምክንያት ካልገጠማቸው። በእርግጥ መንዝ ተቀምጦ የአማራን ስብዕና ያጠናው ሌቪን እንደፃፈው አማራ ርቀቱን ጠባቂ ወይም የግላዊ ሕይወት ተከታይ ነው ይላል። ልጁንም ሲዳር እንደ ኦሮሞ ከጎኑ ቤት አይሰራም። ራቅ ያለ ቦታ እንዲሰራ ያደርገዋል። ዉሻም አለ። ሲመጡ አክ እንትፍ ማለት ግድ ነው። የተጉለት ሕዝብ የጣሊያን ምሽግ በነበረችው በሳሲት ከተማ ሰርቶ ያለ ባህሉ ተጨናንቆ ይኖራል። 

የሳሲት ወጎች ቁጥር 5 የቅዳሜ ገበያተኞች ድብድቦችና ትዝታዎቼ

 የሳሲት ወጎች

ቁጥር 5

የቅዳሜ ገበያተኞች ድብድቦችና ትዝታዎቼ


ስለ እውነት ለመናገር በፊት በፊት ሰዎች ስለ ሳሲት መልካም ሊባል የማይችል ዕይታ ነበራቸው። ይኸውም ከሌላ ችግር የመነጨ ሳይሆን ከፀብ፣ ከግጭትና ከግድያ ጋር የተያያዘ ነው። አስደንጋጩ የሳሲት ገጽታ በአገሬው መካከል እንጂ እንግዶችን ስለማይነካካ አይደናገጡ። በሃያ ዓመታት ልዩነት የተከሰቱ ተመሳሳይ ነገሮችን እንመልከት። አንደኛው ጋሽ ዳምጠው ደጅ በደርግ ጊዜ፣ ሌላኛው ጋሽ ደመቀ ደጅ በ1990ዎቹ የተከሰቱ ናቸው። ጉዳዩ እንዲህ ነው። ፀብ ይነሣል - ያውም ተመጣጣኝ ባልሆኑ ወገኖች መካከል። አንደኛው ወገን ዱላ ይዟል፤ ሌላኛው ጠመንጃ። የትኛው እንደሚያሸንፍ ግልጽ ነው። መሸናነፍ ብቻ ሳይሆን ሟችና ገዳይ መሆን ይከተላል። በሁለቱም የግጭቱ መንስኤ የዱላዎቹ ትዕግስት ማጣት እንደሆነ ሰምቻለሁ። ባለ ዱላ ከባለ ዱላ፣ ባለ ጠመንጃ ከባለ ጠመንጃ የሚጋጠሙበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ስካር ጠባቸውን ሊያባብስ ወይም መንስኤ ሊሆን ይችላል። የጠባቸው ስር መሰረት ከመሬት ወይም ከሴት አይርቅም። በሀብት ሊቀናኑ ወይም በወሬ ሊጣሉም ይችላሉ። ፖሊስ ወይም ተረኛ ታጣቂ ህግ ማስከበሩ አይቀርም። ይሁን እንጂ በብዛት ፖሊሶች ጥይት ሲሰማ ወይም ጠብ አለ ሲባል አይገኙም። ነገሩ ካለቀ በኋላ ተፈልገው ይመጣሉ። የፖሊስ ጭካኔም ከፍ ያለ ነው። በዱላ ሲደበድቡ ርህራሄ የሚባል የፈጠረባቸው አይመስሉም። ሐኪም ቤትም ዘወትር ቅዳሜ ስራ ይበዛበታል። የተፈነከተን መስፋትና ደም ማስቆም መደበኛ ስራቸው ይመስላል። ብዙ ሐኪሞች በብዙዎች ልብ ውስጥ አሉ። ይህን ሁሉ የመጨረሻ ትዕይንት አስቀደምኩ እንጂ ቅዳሜ ጠዋት ገበያተኛው ከየአጎራባች የገጠር መንደሮችና አካባቢዎች ሲመጣ ያለውን ዉበት አልዘነጋሁም። የእህል ምርታቸውን ተሸክመው፣ አዝለው ወይም በአህያ ጭነው በተቻላቸው መጠን ተውበው ከሩቅ በብዛት ሲመጡ ይስባሉ። ወንዶቹም ሴቶቹም ረጅሙን መንገድ ጨርሰው ሳሲት ሲደርሱ ወደየዘመዶቻቸውና ደንበኞቻቸው ቤት ጎራ ብለው ሰላምታ ያቀርባሉ፤ ዉኃ ጥማቸውንም በዉኃ፣ ጠላ ወይም ለስላሳ ይቆርጣሉ። ወግና ጥየቃው ይቀልጣል። በቀጥታ ወደ ገበያ ሄዶ ሸመታውን የሚያከናውንም አለ። የዕለቱ ጉዳይ ከተተኮሰ በኋላ የመጠጡም ሆነ የምግቡ ገበያ ይቀልጣል። ጠላው፣ አረቄው፣ ጠጁ፣ ቢራው ወዘተ ይንቆረቆራል። ጠቡ በስካር ምክንያት የሚመጣ መሆኑን ከዚህ መገመት ይቻላል። ሌሎችም ምክንያቶች አይጠፉም። የቅዳሜ ገበያ ትርዒት (የጋማ ከብቱንና  ጥቂት መኪኖችን ጨምሮ) ሳሲትን ከሚያደምቋት ዋነኛው ነው። 

ቁጥር 6

የሳሲት ማስተር ፕላን ... ይቀጥላል

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...