2018 ኦገስት 6, ሰኞ

የእንትን ብሔረሰብ አባላት እንደሚጠሉት በምን አወቀ?


ነሐሴ 1፣ 2010፡፡

ደብረ ብርሃን፡፡


የኦክስፎርድ የእንግሊዝኛ መዝገበ-ቃላት ለአንድ ነገር የሚኖረን ‹‹ጽኑ ምክንያት-የለሽ ፍራቻ›› ሲል ቃሉን ይበይነዋል፡፡ በስልኬ ያለኝ መዝገበ-ቃላት በበኩሉ ‹‹አመዛዛኝነት በዞረበት ያልዞረ በልክፍት ደረጃ ያለ ፍራቻ›› ሲል ይፈታዋል፡፡ ትርጉሙን እንደዚህ አውቀን ቃሉን ለማወቅ መቻኮላችን ያለና የነበረ ቢሆንም ቃሉን ለአፍታ እናቆየውና ርዕሰ-ጉዳያችንን እንመርምር፡፡ ‹‹ቃሉንማ አውቀዋለሁ! አንተ አሳስተህ ተረጎምከው! እኔ ባለሙያ ስለሆንኩ በተሻለ መጠን አስረዳለሁ!›› ለሚል ሰው የአስተያየት መስጫው ክፍት ነው፡፡



የአንድን የእንግሊዝኛ ቃል ፍቺ በማብራራት ጀመርኩ፡፡ የአማርኛ አቻ አለው ወይስ የለውም ብሎ ለሚጠይቀኝ ሰው መልሴ አይጠፋም ነው፡፡ ቃሏን ዛሬ ከአንድ ቪዲዮ ስሰማት ‹‹ምነው በፖለቲከኞቻችን ዘንድ ተዘወተረች!›› ብዬ ለመምዘዝ በቃሁ፡፡  

‹‹የእንትን ህዝብ ለምንትስ ህዝብ ፎቢያ አለው›› በማለት ንግግራቸውን፣ ሃሳባቸውንና ድርጊታቸውን ምክንያታዊ የሚያስመስሉ ፖለቲከኛን ስሰማ ደነገጥኩ፡፡ ህዝቡ የሰዎች ድምር በመሆኑ ጉዳዩን ወደ ሰዎች ደረጃ አውርደን እንነጋገር፡፡

ፎቢያ ያላቸው ሰዎች እንዴት ልጆቻቸውን ለሚጠሉት ይድራሉ?

ጽኑ ምክንያት-የለሽ ፍራቻ ካለው እንዲጋባ ማን ያስገድደዋል?

የፖለቲካ ጋብቻ መሰላቸው እንዴ!



ጥያቄ ሳላበዛ ወደመሰለኝ መልስና ማብራሪያ ልሂድ፡፡

በመደበኛው የማህበረሰቡ ኑሮ ልጅን ለመዳርም ሆነ ለራስ የትዳር አጋር ለመፈለግ  ሁኔታው በዘላቂነት ተጽዕኖ ያለው በመሆኑ የትዳር አጋር ምርጫው በጥንቃቄ ይፈጸማል፡፡ ይህም በአብዛኛው በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በትውልድ ስፍራ፣ በኑሮ ደረጃ ወዘተ ተመሳሳይነት ያለው ሰው ፍለጋን ያመጣል፡፡ ከህዝብ እንቅስቃሴ፣ ከዓለም ስልጣኔ፣ ከተግባቦት መጨመር፣ ከአገር ምስረታ ጋር የሚያያዙ ምክንያቶች ከማህበረሰብ ውጪ ማግባትን ግድ ይሉታል፡፡ ከዘመናዊነት ጋር የሚመጣ ከአንድ ማህበረሰብ ውጪ ካለ ሰው ጋር የሚፈጸም ጋብቻ በአገራት ደረጃ ይቅርና በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ነው፡፡ የአንድ አገር ሰው የሌላን አገር ሰው አግብቶ በሰላም እንደሚኖር ይታወቃል፡፡ እኛ አገር በተቃራኒው ከስልጣኔ መንበር በየጊዜው እየራቅን ቁልቁል እየወረድን ስለሆነ በማህበረሰባችን ውስጥ ብቻ እየተጋባን እንገኛለን፡፡ ከውጪ አናስገባም ብለናል፡፡ ይህም የሚያሳየው ትናንት የሰለጠንን ዛሬ በአንጻሩ ያቆለቆልን መሆናችንን ነው፡፡ በሃገራችን አንዱ ማህበረሰብ ከሌላው ሲጋባ የኖረው ተዋዶ እንጂ የፖለቲካ ዓላማ ኖሮት አይደለም፡፡ ነገሥታት አድረገውት ሊሆን ቢችልም ግለሰቦች ግን ሊያስቡት አይቻላቸውም፡፡



ጋብቻ ከትስስሮች ሁሉ የላቀው ስለሆነና ፍሬውም ለዘመናት የሚቆይ ስለሆነ መነሻ ምሳሌ አደረግነው፡፡ይሁን እንጂ በሌላ ዘርፍም ቢሄዱ ጉዳዩ ያው ነው፡፡ ጋብቻ ለመፈጸም ድፍረት ያለው የእውነት ይወዳል ማለትም ስለሚቻል ነው፡፡    



አባቶቻችን ያልተማሩ ሞኞች ስለነበሩ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን፣ ኃይማኖታቸውን፣ ማንነታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ ስላደረጉ ብቻ እኔ አላደርገውም የሚሉም አይጠፉም፡፡ ለሰው ልጅ ተፋቅሮ መኖርና ለዓለም ሰላም ካልጠቀመ የኔ ቋንቋ ምንድነው! ማንነቴስ! ኃይማኖቴስ! ተደፍጥጠዋል የሚልም ይኖራል፡፡ ታዲያ አዲስ ማንነት ቢያዝስ ምን ይኮናል?

ህብረተሰቡ ይጠሉኛል ባላለበት ሁኔታ፣ ጠላ የተባለውም እጠላቸዋለሁ ባላለበት ሁኔታ ይጠሉናል ማለት ምንድነው? ለራስ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ህዝብን የሚያጣላ ነገር ከመደርደር የሚያፋቅር ነገር ማምጣት አይቻልም ወይ?

ለፖለቲከኛው መጠየቅ የሚፈልጋቸው ጥያቄዎች አሉኝ፡-

ሀ. በጽኑ እንደሚጠሉ በምን አወቅህ?

ለ. ህብረተሰቡ በየትኛውም ዓለም እንዳለው አንዱ ላንዱ ከሚሰጣቸው ባህሪያትና ቀልዶች በዘለለ የከረረ ነገር አይተሃል?

ሐ. ምክንያት-የለሽ ፍራቻ እንዴት ይኖራል?

መ. አመዛዛኝነት የሌለው ፍራቻ እውነት እኛ አገር በህዝብ ዘንድ አለ?

ሠ. በልክፍት ደረጃ ያለ ፍራቻስ?



አሁን እዚህ እቤቴ በምሽት እየጻፍኩ (ሐምሌ 30፣ 2010፣ ከምሽቱ 7፡17 ላይ) ሳለሁ አንድን ህዝብ ፈርቻለሁ? አልፈራሁም፡፡ ለምን ብዬ? በወገን መሃል ነኝ ብዬ አምናለሁ፡፡

በእንትናችን ምክንያት ይሰድቡናል ሲባል የከረመውን ነገር አንድ ወቅት ከሰው ጋር ባደረኩት ወግ እንደተረዳሁት የሚገርም ግንዛቤ ጨብጫለሁ፡፡ ሰዳቢ የተባለው ህዝብ አንድ አባል የነገሩኝ ነገር ቢኖር ‹‹እነሱ እኮ በእንትናቸው ይኮሩብናል›› የሚል ነው፡፡ ‹‹እኛ እንደነሱ አንትን ባይኖረንም ሰርተን እናገኛለን›› ዓይነት ነገር መሰለኝ ያሉኝ፡፡ ይንቁናል የተባለው ነገር የሚያስከብራችሁ ሆኖ ተገኘ፡፡ ‹‹ጎረቤቴ ይህን ያወራ ይሆናል›› ብሎ ከማሰብ የራስን ሃሳብ መኖር የሚሻል ይመስለኛል፡፡ ያኔ ከተጋነነ ፍራቻ ራሳችን ነጻ እንወጣለን፡፡ ምናልባት እኛው ከሆንንስ የተጋነነ ፍራቻ ያለብን! ራሳችንን እንመርምር፡፡



ከጽሑፉ በኋላ የመጡልኝ ሃሳቦች፡-



ወደ ሌሎች ስንጠቁም አራቱ ጣቶቻችን ወደራሳችን ይጠቁማሉ የሚለው አባባል ለአሁኑ ጉዳያችን ትክክለኛ ማስረጃ ነው፡፡

ይፈሩኛል ብሎ መኖር ምን ጥቅም አለው? እፈራቸዋለሁ ቢሆን የራስን ስሜት ስለሆነ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡

ምን አልባት ፈርተው ከሆነም መፍራታቸው ይጠየቅ፡፡

እውነት ከፈሩ አይዟችሁ በላቸው፡፡

በፍርሃት እንዲሞቱ ብትፈቅድ ግን ዋጋ የለውም፡፡

እኛና አነሱ እያልክ ከምትከፋፍል አርፈህ ስራህን ብትሰራ ምን አለበት

እሱና እኔ ከምትል እኛ ብትል አስደናቂ ጥምረት ይፈጠርና በጋራ ታድጋላችሁ፡፡

የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል፡፡

የጥርጣሬ ቤት ከንቱ አደጋ ይጠብቀዋል፡፡

የበለጠ የፍራቻ ቤት የፈሪ ዱላና ያልተጠበቀ ውድመት ያስከትላል፡፡


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት

  በመንግሥት ወደ ወለጋ ከተወሰዱ በኋላ ዛሬ በግላቸው ደብረብርሃን የገቡት አዛውንት የዓይን ምስክርነት ረቡዕ፣ የካቲት 20፣ 2016 ዓ.ም. መዘምር ግርማ ደብረብርሃን   ዛሬ ረፋድ አዲስ አበባ ላምበረ...