ረቡዕ 8 ኦገስት 2018

ሁሉ አማረሽን ‹ኢንተርኔት› አታውጧት፡፡

መዘምር ግርማ
የእንግሊዝኛ ሥነ-ጽሑፍ መምህር፣ ተርጓሚ፣ የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት መስራችና ባለቤት፡፡
ይህ ጽሑፍ በአምስት መቶ ቃላት የተቀናበረና በሦስት ደቂቃ ውስጥ ተነቦ የሚያልቅ ነው፡፡

እንደ ሕዋ?
አሁን መንፈቀ ሌሊት ሲሆን፤ ደብረብርሃን በሚገኘው ቤቴ ሃሳቦቼን በጽሑፍ እያሰፈርኩ ነው፡፡ ከተወሰኑ ሠዓታት በፊት እንደ ኢትዮጵያ ሕዋ ሳይንስ ማህበር ከፋይ አባልነቴ የደብረብርሃኑ የቅርንጫፍ ማህበራችን ሊቀመንበር መምህር ግዛው ብርሃኑ የሰጠኝን ኮስሞስ የሚል ስለ አጽናፈ-ዓለም የሚያትት ዘጋቢ ፊልም እያያሁ ነበር፡፡ ከዚህ ፊልም ጋርም የሚያያዝ መልዕክት ላደርስዎ ግድ አለኝ፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ኢንተርኔት ወይም በይነ-መረብ እንደ አጽናፈ-ዓለም ባይሆንም ለኛ ግንዛቤ አጽናፈ-ዓለም መሰል ሰው ሰራሽ ትስስር ነው፡፡ እኔና እናንተ ምንም ብንጥር ከአራት በመቶ በላይ የኢንተርኔትን ግዛት መዳሰስ አይቻለንም ይባላል፡፡ ከጥቁሩ (96 በመቶው) ክልል መግባት ፈጽሞ የተከለከለ ነው ይባላል፡፡ ያስቀስፋል፡፡
የሰው ልጅ መጻፍ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ አንድ መቶ ሰላሳ ሚሊየን መጻሕፍትን ጽፏል፡፡ እኛም ይህንን ማንበብ የምንችል አይደለን፡፡ ከዚህም ውስጥ በዚህች ባለችን እውቀትና ችሎታ በየስድስት ወሩ በየቋንቋው በእጥፍ ከሚጨምረው የመረጃ ቋት ስንቱን ማየት ይቻለናል? የጽሑፍ ብቻ አይደለም፤ የምስል፣ የድምጽ፣ የቪዲዮና ከዚህም ውጪ ሠነዶች አሉ፡፡ ዓለም እንዴት አንደዋለች በቪዲዮ የሚቀጸውን ጉግል ኧርዝን እንኳን ስንት ሆነን እንበረብረው ይቻለናል?

ሁሉ አማረሽ?
በእርግጥ እትዬ ሁሉአማረሽ የሚሏት ቆንጆ ተወልጄ ባደኩባት ሳሲት ከተማ አልነበረችም፡፡ እኛ ሰፈር እትዬ ሁሉ ግርጌሽ ነበረች፡፡ ሌላዋ ደግሞ አገሬው ስሟን መጥራት ስለማይችል ‹ሁሉ አገርሽ› የሚላት በሠማይ የምታልፍና ባስፈለጋት ቦታ ማረፍ የምትችል ፍጥረት አለች - ሄሊኮፕተርን መሆኗ ነው፡፡ ሁሉ… ሁሉ… ሁሉ… እያልን ስንሄድ እናንተም አገር የማትጠፋው ሁሉ አማረሽ ነች፡፡  ገበያ ወጥታ ያገኘችውን ዕቃ ስትነካካና ዋጋውን ስትጠይቅ የምትውል ቅንጡ እመቤት! ሁሉም ስለሚያምራት አንዱም ለየት ብሎ አይታያትም፤ አያረካትምም፡፡ ብዙ ቀን ስትመርጥና ሰው ስታደርቅ ውላ ሳትገዛ ትገባለች፡፡ ከስንት አንዴ ገዛችም ከተባለ የረባ ነገር ገዝታ አታውቅም ይባላል፡፡ መጣች ከተባለ ነጋዴ ሁሉ ስራዋንና አድራጎቷን ስለሚያውቅ ይማረርባታል፡፡ ታዲያ አንድ ነጋዴ ለቤተሰቦቿ ‹‹ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት›› ብለው ነገሯቸው፡፡ ስሟም ሁሉ አማረሽ ሆኖ ቀረ፤ እሷም ገበያ መውጣት ተወች፤ ቤተሰቧም ይሆናታል ያሉትን እቃ በጥንቃቄ መርጠው ገዝተው ያመጡላት ጀመር፡፡ ከዚያ ወዲህ ከበፊቱ የተሻለ ምርጥ እቃ ትጠቀም ጀመር፡፡ እድሜ ለቤተሰቦቿ፡፡ ግን እስከመቼ በሰው ተመርጦላት ትገፋዋለች?

ሁሉአማረሽ ኢንተርኔት ትጠቀም ጀመር፡፡
ያቺ ሁሉአማረሽ ትምህርቷን ጨርሳ ኢንተርኔት ትጠቀም ጀመር፡፡ ታዲያ ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይተውም እንደሚባለው ሆነና ያ ችግር መልኩን ለውጦ መጣላት፡፡ እንደሚከተለው እንይላት
ሀ. አንዱን ለመምረጥ የመቸገር ነገር አልለቅ አላት፡፡ ስትነካካና ከስፍራ ስፍራ ስትዘዋወር ትውላለች፡፡ ከድረገጽ ድረገጽ ትሄዳለች፡፡ ለሳይንስ፣ ለቴክኖሎጂ፣ ለፍልስፍና፣ ለዕውቀት ምናምን ቦታ አትሰጥም፡፡ የተለያዩ ጆርናሎችንም ሆነ የምርምር ተቋማትን አትቃኝም፡፡ አንድ ገጽ ላይ ስትገባም በሚያረካ መልኩ አታየውም፡፡
ለ. እንደ ገበያው ይህ የቴክኖሎጂ ገበያ ለየት አድርጎ የሚያወጣላት የምትፈለገው ገጽ የለም፡፡ ዓይኗ ገብቶላት ጊዜ የምታሳልፍበት የለም፡፡ ለብ ለብ ስታደርግ ትውላለች፡፡ የአእምሮ ኳሸርኳር ይዞሻል የሚሏት አሉ፡፡ በልቅምቃሚ መረጃ ስለተሞላች ያወቀች የሚመስላት ጊዜ አለ፡፡
ሐ. ገበያ ላይ ሰው ማድረቋ እዚህም አልቀረም፡፡ በቻቱ በምኑ ሰውን ተደርቃለች፡፡ በመሆኑም ሰዉ ይማረርባታል፡፡ ጊዜ ሰጥታ ብትሰራና ስራዋን አንድ ቀን ቁጭ ብላ ብትገመግም በሙሉም ባይሆን በከፊል ባሻሻለች ነበር፡፡
መ. አንድ ቀን ገበያ መውጣት የምትተው ትመስላለች፡፡ ገዢ እንጂ ሻጭ እንዳልሆነች ይታወቃል፡፡ ገበያ የራሷን የምታወጣው የላትም፡፡ ሰው በጻፈው ላይ ሃሳብ ለመስጠተ ትጣጣር ይሆናል፡፡ አንብባ ትጨርሰውም አትጨርሰው የሆነ ነገር ትላለች፡፡ የራሷግን ምንም የላት፡፡
ሠ. ከእንግዲህ እሷ ይህን መድረክ ወይም ገበያ ስላልቻለችበት በልጅነቷ እንደነበሯት ወላጆች ሁሉ የሚያስፈልጋትን መርጠው የሚያመጡ ሰዎች ስለሚያስፈልጓት በራስሽ ኢንተርኔት ዘንዳ ድርሽ አትዪም ተብላለች እላችኋለሁ፡፡ ጊዜ፣ ገንዘብ፣ ብዙ ሃብት አባከነቻ፡፡ ከሁሉ አገርሽ የምንማረው ነገር ብዙ ስለሆነ ሁላችንም ሃላፊነት የተሞላበት ስራ እንስራ እላችኋለሁ፡፡



     



1 አስተያየት:

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...