ረቡዕ 8 ኦገስት 2018

ጊዜን ፍለጋ ! ጊዜ፣ ብልሆች የሚተጉለት፣ ደካሞች የሚዘነጉት ሐብት


ደራሲ  - ሊዮን ሆ
ተርጓሚ - መዘምር ግርማ

ዕቃን ወይንስ ጊዜን እንግዛ?
በጣም የሚፈልጉትን ነገር ለመጨረሻ ጊዜ የገዙበትን ወቅት ያስታውሱ፡፡ ቆይቶ ምን ተሰማዎት? መቼም ተደስተዋል፡፡ አሁንስ ሌላ በእውነት የሚፈልጉት ነገር አለ? አዲስ ላፕቶፕ፣ ስማርት ስልክ ወይንም አዳዲስ የወጡ ምርጥ ምርጥ ልብሶች? የፈለጉት ዕቃ ምንም ይሁን ምንም እሱን መግዛት ደስታን ያጎናጽፍዎታል፡፡ በመጨረሻም እቃውን በእጅዎ ሲያስገቡ እስኪ ልሞክረው ወይም ልጠቀምበት ብለው በማሰብ ይደሰታሉ፡፡ ምናልባት ‹‹ገንዘብ ደስታን አይገዛም›› የሚለውን ብሒል ሰምተው ይሆናል፡፡  አዎ! ለጊዜው ያንን የምንፈልገውን ነገር ስንገዛ ደስተኞች ልንሆን እንችላለን፡፡ ይሁን እንጂ፡-

ይህ ደስታ የእውነት እንዳይመስልዎት
የሰው ልጆች ጊዜያዊ ደስታን መፈለጋቸው ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው ነው፡፡ ‹ጊዜያዊ ደስታ› የሚለውን አገላለጽ ምናልባት ለመቶዎች ጊዜያት ሰምተውት ይሆናል፡፡ የምንፈልገውን ነገር በፈለግነው ቅጽበት ማግኘት ማለት ነው፡፡ ይህ የ‹ጊዜያዊ ደስታ› ፍላጎታችን የመጣው በምድር ላይ ራሳችንን ለማቆየት በምናደርገው ጥረት ምክንያት ነው፡፡ እዚህ ጋ ዓላማዬ ስለ ጊዜያዊ ደስታ በዝርዝር ለማውራት አይደለም፡፡

‹ጊዜያዊ ደስታ›ን ፍለጋ በሰዎች ልጆች ተፈጥሮ ያለ ቢሆንም እኛ የምንኖረው በ‹ዘገየ ደስታ› በሚመራ ማህበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ የ‹ዘገየ ደስታ› የሚባለው አንድን ነገር ፈልገን በፈለግነው ሠዓት ማግኘት ሳንችል ስንቀር የሚከሰተው ነው፡፡ ደሞዛችን እስኪከፈለን፣ በምንወደው ምግብ ቤት ምግብ እስክንበላ፣ ወይም በትልቅ ሆቴል ቡና እስክንጠጣ በትዕግስት እንጠባበቃለን፡፡ የፈለግነው ነገር ሲደርስ ደግሞ በጣም እንደሰታለን፡፡

ይህንን ነገር ጥበቃ የናፈቅነው ናፍቆት፣ የነበረን ምኞት ወይንም ይህ የዘገየው ደስታ ራሱ ስናገኘው ከሚሰማን በላይ ስሜታችንን ይነካዋል፡፡ ይህን ስሜት የሚያመጣውም ‹ዶፓሚን› ነው፡፡ ዶፓሚን በአእምሯችን ውስጥ ያሉትን የደስታ ቀጣናዎች የሚቆጣጠር ቅመም ነው፡፡ አንድን ነገር በጣም ከፈለጉት፣ በአእምሮዎ ውስጥ በሚካሄደው የዶፓሚን መለቀቅ  ደስታ እየተሰማዎት ነው ማለት ነው፡፡ የሆነው ሆኖ ያ የሚፈልጉት ነገር ግን የአስፈላጊነቱ ደረጃ ወደ ሁለተኝነት ወረደ ማለት ነው፡፡ እስኪ እንዲያው ቆም ብለው ያስቡት፡፡ ለረጅም ጊዜ እገዛዋለሁ በማለት ሲመኙት የነበረውን ነገር ከገዙት ከተወሰኑ ሰዓታት በኋላ ምን ተሰማዎት? መቼም እቃው እጅዎ የገባ ጊዜ የተሰማዎትን ያህል አይደለም፡፡ ሲመኙት የነበረው ጊዜ የነበረዎትንም ደስታ ያህል አይደለም፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ሰው የመሆናችን ውጤት ነው፡፡
ይህ በዚህ መልኩ የሚሰማዎት ደስታ እውነተኛ ደስታ አይደለም፡፡ በእርግጥ ሰውነትዎ ውስጥ ከሚካሄደው ስነ-ሕይወታዊ እንቅስቃሴ አንጻር ስናየው የሚደሰቱት በዶፓሚን ርጭት ምክንያት ነው፡፡ ይህ የዶፓሚን ርጭት ሲያበቃ መልሰው ሌላ አዲስ ነገር የመፈለግ እድልዎ ሰፊ ነው፡፡ የዚህም ምስጢሩ የበለጠ ዶፓሚን ፍለጋ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ገንዘብ ደስታን አይገዛውም›› የሚለው ነባር አባባል ትክክለኛ ትርጉሙ እንግዲህ ይህ መሆኑ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ገንዘብ ደስታን የሚገዛልዎ መንገድም አለ፡፡ ችግሩ እርስዎ በሚያስቡት መንገድ አይደለም እንጂ፡፡


ደስታን ከፈለጉ ጊዜን ይግዙ

የአሜሪካ ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ በቅርቡ ባሳተመው መጽሔቱ የአንድን ጥናቱን ውጤት አቅርቦ ነበር፡፡ ለጥናቱም በሁለት ቡድኖች የተከፈሉ ሰዎች እያንዳንዳቸው ለየግላቸው አርባ አርባ ዶላር ተሰጣቸው፡፡ የአንደኛው ቡድን አባላት በገንዘቡ ማናቸውንም የፈለጉትን እቃ እንዲገዙበት ተነገራቸው፡፡ የሁለተኛው ቡድን አባላት በአንጻሩ የበለጠ ነጻ ጊዜ እንዲኖራቸው የሚያስችላቸውን እድል እንዲፈጥሩበት ተነገራቸው፡፡ ለምሳሌ ምግብ ከሚያዘጋጁ ይልቅ ተሰርቶ እንዲመጣላቸው እንዲያስደርጉ፣ ወይንም ቤታቸውን ራሳቸው ከሚያጸዱ ይልቅ ሌላ ሰው እንዲያጸዳላቸው እንዲያስደርጉ ታዘዙ፡፡ የጥናቱ ተሳታፊዎች እያንዳንዳቸው ደስታቸውን ከዜሮ እስከ ዐሥር ባሉት ቁጥሮች ተጠቅመው እንዲመልሱ ሲደረግ  ገንዘቡን ተጨማሪ ነጻ ጊዜ በመግዛት ላይ ያዋሉት ሰዎች እቃ ከገዙቱ ይልቅ በአንድ ሙሉ ነጥብ ልቀው ተገኝተዋል፡፡     

የተደሰቱት እንግዲህ መስራት ከማይፈልጉት ነገር ራሳቸውን በማላቀቃቸው ነው፡፡  በረጅም ጊዜ ሲታይ ገንዘቡን ተጨማሪ ጊዜ ለመግዣ ያዋሉት ሰዎች የላቀ የህይወት እርካታ ሲያገኙ፤ ተጨማሪ ሸቀጥ መሸመቱ ግን በእነዚያኞቹ ደስታ ላይ ያመጣው ለውጥ አልነበረም፡፡  

ሰዎቹን ያስደሰታቸው ያገኙት ነጻ ጊዜ ነው፡፡
ያ ያገኙት የጊዜ ፋታ ነው ደስታቸውን ያመጣላቸው፡፡ ገንዘቡ በቃ ተጨማሪ ጊዜ ለማግኘት የተጠቀሙበት መሳሪያ ነው፡፡ ገንዘቡ በመሰረቱ አላስፈላጊ ነው፡፡ ዋናው ቁም ነገሩ ጊዜን የሚያዩበትን መንገድ ማስተካከሉ ላይ ነው፡፡

እያንዳንዳችን በቀን 24 ሰዓት አለን፡፡ [በበለጸገው ዓለም?] የሴቶች አማካይ የእድሜ ጣሪያ 81.2 ዓመት ሲሆን፤ የወንዶቹ ደግሞ 76.4 ነው፡፡ ከሞላ ጎደል አብዛኞቻችን እኩል ጊዜ አለን ለማለት ይቻላል፡፡ እያንዳንዷ ሰዓት ወይንም ደቂቃ በአስፈላጊው ነገር ማሳለፍ መቻል ደስተኛ ህይወትን የመፍጠሪያው ዓይነተኛ መንገድ ነው፡፡
እርስዎ ሁልጊዜ ብትለት ወይንም የስራ ጫና የሚሰማዎት ከሆነ፣ ለራስዎም በቂና የተስተካከለ ጊዜ ያለዎት ካልመሰለዎት ሁኔታውን ለማስተካከል ለውጥ ማምጣት ይኖርብዎታል፡፡     


ገንዘብ ይኑረኝ ወይንስ ጊዜ?
ጊዜ አላቂ ነው፡፡ እያንዳንዳችን በዚህ ዓለም ላይ ያለነው በጊዜያዊነት ነው፡፡ ጊዜን በብልሐት መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ምንም የማይጠቅሙዎትን ነገሮች በመፈጸም ጊዜዎትን ሊያባክኑ መቻልዎት እሙን ነው፡፡  ብዙዎች ሰዎች ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት መንገድ ይህ ጊዜያቸው ምንም ገደብ የለውም አንዴ የሚያሰኝ ነው፡፡ ነገሩ ግን በተቃራኒው ነው፡፡
እስኪ በየቀኑ ዐሥር ዐሥር ብር ይቆጥባሉ ብለን እናስብ፡፡ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ 3650 ብር ይኖርዎታል፡፡ በተመሳሳይ መንገድ ከጊዜ በኋላ የሚጠቀሙበት ዐሥር ደቂቃ በየቀኑ ቢያስቀምጡ በዓመቱ መጨረሻ 60 ሠዓታት ይኖሩዎታል፡፡
የእርስዎ ምርጫ ታዲያ የቱ ነው?
አብዛኛው ሰው ገንዘቧን ይመርጣል፡፡ ይገባናል፡፡ ሰዎች ተጨባጭ ነገር ይፈልጋሉ፡፡ ገንዘብም በተፈጥሮው ልንቆጥበው የምንችለው ነው፡፡ ብናጣው ደግመን ሰርተን ልናገኘውም እንችላለን፡፡ የጊዜ ነገር ግን ወዲህ ነው፡፡ አንዲት ሠዓት ካለፈችን ለዘላለሙ አልፋ ትቀራለች፡፡ አብዛኞቹ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚዘነጉት ነገር ቢኖር እነዚያ የተከማቹ 60 ሠዓታት ከ3650 ብሩ የበለጠ ዋጋ ሊኖራቸው መቻሉን ነው፡፡ ጊዜያችንን በትክክል ዋጋ እንሰጠው ዘንድ በአእምሯችን ውስጥ ተጨባጭ ወደሆነ ነገር ልንቀይረው ግድ ይለናል፡፡

ገንዘብ ተጨባጭ ሆኖ ጊዜ ተጨባጭ አይደለም?
ሕይወታችን የተለያዩ ክንውኖች ድምር ነው፡፡ እያንዳንዷን የምንለፋለትን ነገር የምናደርገው በመጨረሻ በጎ ዓላማ አስቀምጠን ነው፡፡  ማንኛችንም ብንሆን ከማያስደስቱ ይልቅ ብዙ አስደሳች ጊዜያት እንዲኖሩን እንፈልጋለን፡፡ ለምንወዳቸውም ይህንኑ እንመኛለን፡፡
እነዚህን ነገሮች ለማገኘት የሚከፍሉት ዋጋ ግን ምንድነው?
ያ ዋጋ ጊዜ ነው፡፡ እያንዳንዱ ነገር የሚደረገው መቼም ለዚህ ሲባል ነው፡፡ አንድን ነገር የምናደርግበት ጊዜ ከሌለን ያ ነገር ትርጉም አልባ ነው፡፡ ቢሊየነር ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ያንን ለማጣጣም ያለዎት ግን አንዲት ሠዓት ብቻ ከሆነች ቢሊየኑ የስሙን ያህል ዋጋ የለውም፡፡
ገንዘብን እንዴት እንደምናገኝና እንደምናጣ በይበልጥ ይገባናል፡፡  ለአብነት አንዲት መቶ ብር መሬት ላይ ብትጥሉ ወዲያውኑ ተመልሳችሁ እንደምታነሷት እርግጥ ነው፡፡ አንድ መቶ ደቂቃ ያለምንም ስራ ብታሳልፉ ግን መቼም ምንም አይመስላችሁም፡፡
የጊዜን ውሱንነት ብናውቅም ብዙውን ጊዜ ውሱን እንዳልሆነ ነው የምናስበው፡፡ አንድ መቶ ብር በጀት እያለዎት አንድ መቶ ሽህ ብር ወጪ ማውጣት እንደሚያከስርዎት እሙን ነው፡፡ ጊዜን እንዲህ ማድረግ ግን የበለጠ ይጎዳዎታል፡፡
‹‹ሌሎች ዕቅዶችን በማቀድ ላይ የምታጠፋው ጊዜ ሕይወት ይባላል፡፡›› ጆን ሌነን፡፡
ገንዘብ ይህን ያህል ተጨባጭ የሚመስለን እኮ በዙሪያችን ያሉት ነገሮች በሙሉ የገንዘብ ዋጋ ስለተተመነላቸው ነው፡፡ የነገሮችን አንጻራዊ ዋጋ ለመተመን ይጠቅመናል፡፡ ለጊዜም ግን ይህን ማድረግ እንችላለን፡፡


ጊዜን የመለኪያው ትክክለኛው መንገድ
አንድ ቀን 24 ሠዓታትን ይይዛል፡፡ ሁሌ በሠዓት ውስጥ ስድሳ ደቂቃ፣ በደቂቃም ውስጥ ስድሳ ሴኮንዶች አሉ፡፡ አንዳንድ ሕይወት ረጅም፣ አንዳንዱ ደግሞ አጭር ቢሆንም እርስዎ ግን ከ70 እስከ 80 ዓመት ዕድሜ ይኖራሉ ብለን እናስብ፡፡ ከዚህ ውስጥስ ምን ያህሉን በወጣትነትና በመልካም ጤንነት ያሳልፋሉ? ከነዚህ ዓመታት ውስጥ በሕይወትዎ ዋጋ ከሚሰጧቸው ሰዎች ጋር የሚያሳልፏቸውስ ስንቶቹን ነው?
ጊዜን በደቂቃዎች ወይንም በሰዓታት እንደሚለካ ነገር ከመቁጠር ይልቅ እንዴት እናሳልፈዋለን የሚለውን መመልከት ይጠቅማል፡፡ የሕይወትዎ ጥራት የሚለካው በጊዜዎ ጥራት ነው፡፡ እርስዎም በአንድ አቅጣጫ ከሚያዩት ይልቅ በበለጠ አተያይ ሊያዩት ይገባል፡፡
እስኪ ለምሳሌ ራስዎን የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይጠይቁ፡-
በቀን ውስጥ ስንት ሠዓታትን ተናደው፣ ሰግተው፣ እርካታ አጥተው ወይንም ተበሳጭተው ያሳልፋሉ?
ከሚወዷቸው ጋር ዝም ብሎ እቤት ውስጥ አብረዋቸው በመቀመጥ ሳይሆን በጥሩ ግንኙነት ምን ያህል ጊዜ ይቆያሉ?
ራስዎን በማሻሻል ስራ ላይ በየቀኑ ወይንም በየሳምንቱ ምን ያህል ጊዜ ለማሳለፍ አስበዋል?
እንዲያው በማይረዷቸው ምክንያቶች የማያስደስቱዎትን ስራዎች በመስራት የሕይወትዎን ምን ያህል ሠዓታት ይፈጃሉ?
በአንድ ምሽት ከ6 እስከ 8 ሰዓታት ያህል በእንቅልፍ እናሳልፋለን፡፡ ግን ምን ያህል ሠዓታት ናቸው እውነተኛ ረፍት የሆኑት? ስለዚህ ምን ያህሉን እንዲያው አልጋችን ላይ ተጋድመን አሳለፍናቸው?

ለእነዚህና እነዚህን ለመሳሰሉ ጥያቄዎች መልስ የሚፈልጉና እርምጃ የሚወስዱ ከሆነ የራስዎን ሕይወት ጥራት ለመቆጣጠር በሚያስችልዎት መንገድ ላይ ሊገቡ ነው ማለት ነው፡፡  ካልሆነ ግን ለመጀመር ጊዜው አሁን ነው፡፡
ስራዎትን ትተው እያንዳንዱን ቀን እንደፈለጉ እንዲያሳልፉ እየመከረኩዎት አይደለም፡፡ ያ ምክንያት-አልባና የማይመስል ነገር ነው፡፡ ስለነገሮች እንዴት ማሰብ እንዳለብዎትና ምን ላይ ለማተኮር እንደሚወስኑ በየቀኑ ሊመርጧቸው የሚችሏቸው በርካታ ምርጫዎች አሉልዎት፡፡ እርስዎ ልብ አሉትም አላሉት እነዚህን ምርጫዎች ሁልጊዜ ይመርጣሉ፡፡ እነዚህን ምርጫዎች ልብ ብለው ሕይወትዎን የሚቆጣጠሩ ከሆነ ትርጉም ያለው ጊዜ የሚያሳልፉባቸውን በርካታ ሠዓታት፣ ቀናት እንዲሁም ዓመታትን ይቀዳጃሉ፡፡ እያንዳንዱ ሰው በየቀኑ ተመሳሳይ ሃያ አራት ሠዓት አለው፡፡ ቢሆንም እርስዎ ግን ከሚያስቡት በላይ ከዚህ ጊዜ አብዛኛውን በቁጥጥርዎ ስር ማዋል ይችላሉ፡፡
የመጀመሪያው እርምጃዎ መሆን ያለበት ጥራት ያለውን ሕይወት ዝም ብሎ ለንግግርዎ ማሳመሪያ ሳይሆን እውነተኛ እሴት ለማድረጊያ መጠቀም ይኖርብዎታል፡፡   
በመሰረቱ የሕይወትዎ ጥራት የሚበየነው በጊዜዎ ጥራት ነው፡፡
የእንቅልፍዎን ጥራት በእጅጉ የሚያሻሽሉ ትናንሽ ተግባራትን በቀኑ ውስጥ ቢወስዱ ምን ይመስልዎታል?
አለያም የሃያ ደቂቃ የቀን እንቅልፍ በመተኛት የዕለቱን ምርታማነትዎንና የሰውነትዎን አቅም ያሳድጉ፡፡
ከጓደኞችዎና ከሚወዷቸው ጋር በሚገናኙባት አጭር ጊዜ ጥልቅ ትስስር ያለው ቆይታ ቢያሳልፉስ?  
እነዚህ እንግዲህ ከላይፍ ሃክ ዋና እሴቶች አንዱ የሆነውን የጊዜዎን ጥራት መጨመርን አስመልክቶ ካከማቸናቸው በርካታ መንገዶች እጅግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በህይወታችን ካሉን ትልልቅ ቁጭቶች የተወሰኑት ጊዜያችንን ለማሳለፍ በወሰንባቸው መንገዶች ምክንያት ያጣናቸው ዋጋ ያላቸው ጊዜያት ናቸው፡፡ እነዚህን ጊዜያት መልሰን ለመኖር ወይንም የተለዩ ምርጫዎችን ለማድረግ እንችል ቢሆን ልንከፍል የምንችለውን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አስቡት፡፡ ስለዚህ ጊዜዎ በትክክል ዋጋ እንዲኖረው የማድረግ ምርጫን ያድርጉ፡፡ አሁን በሕይወት ሳሉና እየተነፈሱ ሳለ፤ አጅግ ዘገየሁ ብለው አያስቡ!  

በበርካታ ክፍሎች ይቀጥላል!









ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...