ሰኞ 6 ኦገስት 2018

የተማረው ወደ ትውልድ ቀዬው ያለመመለሱ ሲፈተሽ


የራስ አበበ አረጋይ ቤተመጻሕፍት የዕለቱ መልዕክት


ነሐሴ 1፣ 2010፡፡

ደብረ ብርሃን፡፡

የጽሑፉ ዓላማ፡- ሁላችንም ‹‹እሱ እኮ የዚህ አገር ልጅ ነው!›› የሚለንን መጥቀምና ማገዝ እንዳለብን ለማስታወስ ነው፡፡   

‹‹በየትኛው የአገራችን ክፍል የተማረው ሰው ወደ ቀዬው ተመልሶ ለውጥ ለማምጣት ቻለ?›› ብለን አእምሯችንን ለመፈተሽ እንሞክር፡፡

ይህን አረፍተነገር ቃል በቃል እንመንዝር ብንል  እንኳን ብዙ ቁም ነገሮችን ማውጣት እንችላለን፡፡ 

ሀ. በየትኛው የአገራችን ክፍል?

ይህን ሃሳብ ስንመነዝረው ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፣ ከጎሬ እስከ ጎዴ፤

ከገጠር እስከ ከተማ፤

ከለማ እስካልለማ፤

ለመድረስ ከሚያዳግት እስከ ምቹ፤

የተለያዩ ኃይማኖቶች፣ የሥልጣኔ ደረጃዎች፣ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና አመለካከቶች ያሏቸውን

የትኛውንም ዓይነት ክፍል ማለታችን ነው፡፡

ለ. የተማረው ሰው?

በህብረተሰቡ ‹‹የተማሩት ምን አመጡ?›› የምንባለውን፤

በአካባቢያችን ያለውን የትምህርት ደረጃ አልፈን ለትምህርት ሲባል የወጣነውን፤

ሰርተፊኬት፣ ሌቭል 1፣2፣3፣ ወዘተ፣ ዲፕሎማ፣ ዲግሪ፣ ማስተርስ፣ ፒኤች ዲ፣ አጫጭር ስልጠና ወዘተ ያለንን

በትምህርት እንጀራ የወጣልንን፤

የሚያውቀን ታዳጊ እንደሱ/ሷ ተምሬ ትልቅ ደረጃ እደርሳለሁ የሚለንን፤

ማለታችን ይሆን?

 ሐ. ወደ ቀዬው?

ዘር ማንዘራችን ከተወለድንበት ሥፍራ የሚመዘዘውን፤

ወላጆቻችን በአካባቢው የተወለዱትን፤

ወላጆቻችን ለሥራ ጉዳይ በሄዱበት የተወለድነውን፤

አካባቢውን አድገንበት ትዝታውና ውለታው ያለብንን፤

ዘለግ ላለ ጊዜ የሰራንበትን፤

ውኃውን የጠጣነውን፤

በንገዱ ያለፍን ያገደምንበትን፤

ትዝታው ውል የሚልብንን፤

እልቆ መሳፍርት ነገር ልናነሳለት የምንችለውን ማለት እችል ይሆን?

መ. ተመልሶ?

ቋሚ መኖሪያውን ወደዚያች ስፍራ ቀይሮ፤

በልቦናው ወይም በእግረ-ህሊናው ሄዶ፤

ረዘም ላለ ጊዜ ሄዶ ቆይቶ፤

ለአጭር ጊዜ ሄዶ ሰርቶ፤

ለአንዲት ቀን ሄዶ፤

ሠ. ለውጥ ለማምጣት ቻለ?

ጫማ እያላችሁ ያለማድረግ ልማዳችሁን ተዉ ካለ፤

ሃሳቡን ካጋራ፤

ካወያየ፤

ግጭት ከፈታ፤

ትምህርት ቤቱን ተመልሶ ካየ፤

የእምነት ተቋሙን ካሰራ፤

ዛፍ ከተከለ፤

ችግረኛን ከረዳ፤

የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ካስተዋወቀ፤

ሌላው ቢቀር በመንደሩ ሄዶ ከተንጎራደደ (እንደሱ እሆናለሁ የሚሉ ልጆች ሊወጡ ስለሚችሉ)፤

ምርጫ ከተወዳደረ፤

ቆቅና ጅግራ ካደነ፤

ግብረ ሰናይ ድርጅት ካመጣ፤

ስልጠና ከሰጠ፣ ካሰጠ፤

በገቢ ማመንጫ ቡድን ካደራጀ፤

ዝርዝሩ አያልቅ ብሎን እንቸገር ይሆን?



ወገኖቼ፣

ወገኖቼ ማለቴ ላቀርባችሁ ስለምችል፣ ስለምወድ፣ ስለሚገደኝ፣ ስለማይቆጨኝ፣ መልካም የሆነው ሁሉ ወዘተ ነው፡፡

ቀስ ብለው ራስዎን ይዘው ይከተሉኝ፡፡

በምናብ፡፡

አንድ አፍታ፡፡

ከተቻለ በዚያች ቀዬ አብሮዎት ላደገ ሁነኛ ወዳጅዎ ይህን ጽሑፍ ይላኩለት፤ አንብቦም ተወያዩበት፡፡ አንድም ነገር አድርጉ፡፡



በዚያች ቀዬ አካላዊ ትዝታ፡-

አፈሩን ሲፈጩ የነበረው፤

በባዶ እግርዎት ሲሄዱ የነበረው፤

ፀሐይ ላይ ሲቀመጡ የነበረው፤

ሲያምዎት የነበረው፤

ሲርብዎት የነበረው፤

ሲጠግቡ የነበረው፤

ቀን የሚውሉባቸው ስፍራዎች፣ አመሻሽ የሚያሳልፉባቸው የተለመዱ ቦታዎች፣ ሌሊት የሚያድሩበት ቦታ (አልጋ፣ ድብዳብ፣ መደብ፣ መሬት፣ ሳጥን ላይ፣ ምድጃ ….)

መጸዳጃ ቤት ነበር ወይስ አልነበረም?

ወሳኝ የህይወትዎ ጊዜያትስ - ልደት፣ ግርዘት፣ ክርስትና፣ ሰርግ፤



በዚያች ቀዬ መንፈሳዊ ትዝታ፡-

ቤተክርስቲያናችሁ፣ መስጊዳችሁ፣ የአምልኮ ዛፋችሁ፤

መንፈሳዊ አባቶቻችሁ፤

የበዓላት ቀናት፤

ስታዝኑ፤ ስትደሰቱ፤

ጾምና ጸሎቱ፤

የቡድን አምልኮው፤

ለተቸገረ ያበላችሁበት፤

የተጣላ ያስታረቃችሁበት/የታረቃችሁበት፤

አምላክ ተቀይሞኛል የምትሉበት፤

አምላክን የተቀየማችሁበት፤



በየዘርፉ በርካታ ትዝታ ያላችሁ ያች ቀዬ አሁን በምን ዓይነት መልኩ ተለውጣለች? ‹‹እኔ አካባቢዬን መለወጥ እችላለሁ›› ብለን ማመን አለብን ይህን ጉዳይ ከዳር ለማድረስ፡፡ ተስማማን መሰለኝ፡፡ እንቀጥል፡፡ የተወሰኑ ዘርፎችን ለይተው እርስዎ ሲያድጉ ከነበረው የተሻለ ለማድረግ የድርሻዎትን ይወጡ፡፡

ምን ምን ሊያሻሽሉ እንደሚችሉ እንነጋገር፡፡

ሀ. ሰፈራችሁ

ለ. ትምህርት ቤታችሁ

ሐ. የእምነት ተቋማችሁ

መ. ማህበራዊ ግንኙነታችሁ

በእነዚህ ዘርፎች አንድ አንድ ነገር ለመስራት ከተነሱ ሌላውም እየተሰካካ ይፈታል፡፡ ጓደኞችዎ ደግሞ ከእርስዎ የበለጠ የጋለ ስሜት ስላላቸው በአራት ዘርፈፎ እንዲሁ መስራት ይቻላቸዋል፡፡



ያኔ

የሥልጣኔ ጮራ እናንተ ቀዬ ሰተት ብላ ትገባለች፡፡

የሰራችሁትን ስለምትጽፉት ሌሎችም ይከተሏችኋል፡፡

ጸጸት አይኖርብዎትም፡፡

በሌሎች የህይወትዎ ዘርፎች ስኬቶችን ይቀዳጃሉ፡፡

ውለታ ቢስነት አይሰማዎትም፡፡



ለተግባር ስለተነሳሱ አመሰግናለሁ፡፡



ከጽሑፍ በኋላ የመጡ ሃሳቦች፡-

ሀ. በኢትዮጵያ ሬዲዮ በአንድ ወቅት የሰማሁት ሰው ሃገር ውስጥ ቀርቶ ለመስራትና ለእረፍት ሲል ጥሎት ወደመጣው ውጪ አገር ላለመሄድ የወሰነው ከሃያ ዓመታት በፊት ቁጭ ብሎ ጫማ የሚያስጠርግበት ድንጋይ በመጣም ጊዜ እዚያ ስፍራ መኖሩ አሳዝኖትና የቀዬውን ያለመለወጥ አይቶ ነው፡፡

ለ. የህይወት መንገዱ የጠፋቸውና እኛ አንድ አፍታ ችግራቸውን አይተን ብንመክራቸው ሊለወጡ የሚችሉ የልጅነት ጓደኞችና የምናውቃቸው ሰዎች አሉ፡፡ የባንግላዴሹ ማህሙድ የኑስ የሚሊዮኖችን ህይወት እንዴት እንደለወጡ አንብቡ፡፡

ሐ. እኛን ያዋለዱን እናቶች የት ይሆኑ? እንደኛ ልጅ አላቸውን?

መ. ለትምህርት ቤታችን ለዓመት ማስታወቂያ መጻፊያ የሚበቃ ማርከር ከ100 ብር የሚበልጥ አይመስለኝም፡፡
 


ምንም አስተያየቶች የሉም:

አስተያየት ይለጥፉ

የጃዋር መሐመድ 'አልፀፀትም' እንደ ባራክ ኦባማ 'The Audacity of Hope'?

'አልፀፀትም' የተባለው የጃዋር መሐመድ መጽሐፍ ወደ መደምደሚያው ዲሞክራሲን በኢትዮጵያ ለማምጣትና አገረመንግሥቱን ከውድቀት ለመታደግ ይጠቅማሉ የሚላቸውን ሐሳቦች ይጠቁማል። ይህን ግን ደጋግሞና በስፋት ካቀረበው...