በደብረብርሃን ዩኒቨርስቲ ስለተከሰተው ሁኔታ ማለትም ስለ አራቱ ኮሌጆች መዘጋት በአካልም ሆነ በውስጥ መስመር ለጠየቃችሁኝ ወገኖቼ ማብራሪያ ለመስጠት ሞክሬያለሁ።
ለሌሎቻችሁም ለማጥራት ያህል
1. እኔ በጉዳዩ ላይ ከአሁን በኋላ የለሁበትም በሚል ያሳወቅሁትን አስመልክቶ
ሀ. ጉዳዩን የተመለከተ ጥያቄም ሆነ ሙግት ውስጥ አልሳተፍም።
ለ. ዩኒቨርስቲው ትሰራለህ እስካለኝ እሰራለሁ። አትሰራም ሲለኝ እሄዳለሁ። የት? የሚለውን አልወሰንኩም። ምናልባት እዚሁ ደብረብርሃን ቆይቼ አገለግላለሁ። ወይም ወደ ሳሲት (እነሱ ካቅማሙ ሌላ ወረዳ) ሄጄ ከታች ወደ ላይ የሚመጣና እርዳታ የማይቀበል ህብረተሰብ ተኮር ፕሮጀክት አስተዋውቃለሁ።
2. አማርኛ መምህር ነህ ወይ? ለተባለው
አማርኛ መምህር አይደለሁም። የመጀመሪያ ዲግሪዬ በእንግሊዝኛ ሲሆን፤ አማርኛን በንዑስነት ተምሬያለሁ። መመረቂያ ጽሑፌ በአማርኛ መጽሐፍ ላይ ሲሆን የመመረቂያ ጽሑፉን የጻፍኩት በእንግሊዝኛ ነበር። በማስተርስ ደግሞ ሁለት የአማርኛና ሁለት የእንግሊዝኛ መጻሕፍት ላይ መመረቂያዬን ጽፌያለሁ። አንድ የትርጉምና ሁለት የራሴን መጻሕፍት በአማርኛ አሳትሜያለሁ። በአማርኛ መጻፍ ያስደስተኛል። ብሎግም አለኝ። በዩኒቨርስቲው ውስጥ በነበረው ባህል ማዕከል በመጻፍ፣ በመወያየትና ሃሳብ በማግኘት ተጠቅሜያለሁ። ከአብያተመጻሕፍቱ፣ ከመምህራኑ፣ ከሰራተኞቹና ከተማሪዎቼ ተምሬያለሁ። እንግሊዝኛ በተለይም ሥነጽሑፍ የሚያስተምር መምህር እንደመሆኔ መጠን ለአማርኛ ቋንቋና ሥነጽሑፍ በጣም ቅርብ ነኝ።
3. ከሥራ መባረሩ ያሰጋሃል ወይ?
በቅርቡ በተዋወቀው መርሐግብር መሠረት አሁኑኑ አልባረርም። የኔ ግምት ከአማርኛ ቀጥሎ የኔ ትምህርት ክፍል (እንግሊዝኛ) በቀጥታም ባይሆን በሌሎች ስብሰባዎች ፍንጭ ተሰጠ እንደተባለው ተጠቂ ነው። ወደ እንግሊዝኛ ስንመጣ አራት የትኩረት ዘርፎች አሉ። እነሱም እንግሊዝኛን ማስተማር (TEFL)፣ ሥነልሣን፣ ጋዜጠኝነትና ተግባቦት እና ሥነጽሑፍ ናቸው። በእኔ ግምት ከእንግሊዝኛን ማስተማር (TEFL) ዉጪ ያለው ተቀናሽ ነው። ስለዚህ እኔ የሥነጽሑፍ መምህር ስለሆንኩ እቀነሳለሁ። ከTEFL መምህራን ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪ የሌላቸው ይቀነሳሉ። ያንን ታስቦ መሰለኝ አምስት መምህር ይቀራል የተባለው። በግሌ ሦስተኛ ዲግሪ ለመስራት አልፈልግም። ይህንን ማስተርስ ሳልመረቅም አውቀዋለሁ። ዩኒቨርስቲ ውስጥ መቆየት አለመፈለጌ ነው አንደኛው ምክንያት። እሄዳለሁ ያለ አይሄድም እንደሚባለው ሳልሄድ ብዙ ጊዜ ቆየሁ። ታዲያ ከዩኒቨርስቲ ባሻገር ምን ለመስራት አሰብክ ከተባለ እሱን አሁን ከላይ ከተጠቀሰው ውጪ መደምደም አልችልም። ሲደርስ እናወጋበታለን።
3. በጀመራችሁት ዩኒቨርስቲውን ወደ ትክክለኛ መንገድ የማምጣት ሂደት ተሸንፋችሁ ነው ወይ?
ኧረ በፍፁም። ጉዳዩ ደህና ሄዶልናል። ሁሉም መምህር በትጋት ጠበቅ አድርጎ ከያዘው ዩኒቨርሲቲውን ወደ መልካም መንገድ የሚወስደው ይሆናል። በቅርብ ዓመታት ጠንካራ ዩኒቨርስቲ እንደሚኖረን ይታየኛል። ስህተቱም ይታረማል።
4. ቤተመጻሕፍትህስ?
ቤተመጻሕፍቴ ምንም አይሆንም። ቢሆንም ችግር የለውም። ማሳየት ያለበትን ለሰባት ዓመታት ሰርቶ አሳይቷል። በአዲስ ቤት ሥራ መጀመር፣ በርካታ መጽሐፍ መጨመር፣ ፈንድ ማፈላለግ የመሳሰሉትን ሃሳቦች አያስተናግድም። ባይሆን እሱን መሰል በየወረዳው ማስተዋወቅ ላይ ይሰራል። ምን ይሰራ የሚለውን ለማጥኛ እየተጠቀምኩበት ነው።
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ