የሳሲት ወጎች
ቁ. 15
የሳሲት ሰው የዕለት ውሎ
(በረቂቅ ደረጃ ያለ፤ ሃሳብ ስጡበት፡፡)
ይህን ክፍል ለማሰብ ከባድ እንደሚሆን ትረዱኛላችሁ፡፡ የአንድን የሳሲት ሰው ብቻ የዕለት ውሎ ቢሆን መጻፍ ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ቅሉ፣ የአማካዩን ሰው መጻፉ ግን አዳጋች እንደሚሆን ለመገመት አያዳግትም፡፡ የእትዬ ስመነን፣ የአሸብርን፣ የአብዬ ጣሰውን፣ የግሩምን ወይንም የቅስርን የዕለት ውሎ መጻፍ ምንም አያደክምም፤ አያሰለችም ወይም አያዳግትም ብለን እናስብ እንዴ? እናንተ ይቻላል፤ ቀላልም ነው ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ እኔ ግን የእነዚህን እንኳን የእለት ውሎ ለመጻፍ ከባድ ይሆንብኛል፡፡
‹‹ኧረ ተው እንዴትም አድርገህ ንገረን›› አልሽ እንዴ እትዬ እታገኘሁ፡፡ ገና ለገና እናንተ ለወሬ ትቸኩላላችሁና የማይውሉትን ውሎ እናገራለሁ እንዴ! ‹‹የማልውልበትን ጻፈብኝ፤ የማላደርገውን አስደረገኝ›› ብለው ቢቀየሙኝስ?
‹‹በኔ ይሁንብህ አይቀየሙህም››
‹‹ስትይ፣ ዋስ ትሆኝኛለሽ?››
‹‹መጠርጠሩስ!››
‹‹መግደላይትን በይ››
‹‹አባቴ ይሙት››
‹‹ጉድ ስማልኝ ጋሽ ደምሴ››
‹‹ምን አልከኝ?››
‹‹ወግ አውጋልኝ ብላለች አወጋለሁ፡፡››
‹‹ታዲያ ምን ቸገረኝ››
‹‹አይ እኔ የሳሲት ሰው የዛሬ ሃያ ዓመት እንዴት ውሎ እንደሚያድር ልናገር ነበር፡፡››
‹‹ጠንቋይ ነህ እንዴ?››
‹‹ሲያልፍም አይነካካኝ››
እኔ ሳሲቶች ጋ አንድ ሰው እንዴት ውሎ ያድር እንደነበር ተናግሬ አልቀያየምም፡፡ ረስተውትስ ቢሆን፡፡ ያልሆነውን ሆነ አልክ እንዳይሉኝ፡፡ ነገሩ ከባድ የሚሆነው እንዴት መሰላችሁ፣ የጓደኛዬን የግሩምን እንኳን በምናቤ ልስለው አልችልም፡፡ ስለዚህ የአምስት የሳሲት ሰዎችን የዕለት ውሎ እንጨፍልቅና ለአንዲት ማንያዛታል ለተባለች ሴትዮ እንስጣት፡፡ ሁሉንም ባይወክልም የውሱን ሰዎች አማካይ መሆን ትችላለች፡፡
እንደማንኛውም ሰው በጠዋት ትነሳለች፡፡ ሜዳ ትወጣለች፡፡
‹‹የምን ሜዳ?›› አልከኝ?
አይ አንባቢ፡፡ ሜዳም አታውቅ!
ሜዳ ማለት መጸዳጃው ነው፡፡ እንደዛሬ ሽንት ቤት የለም፡፡ መጸዳጃው ሜዳ ላይ ነው፡፡ ሰው ሳይበዛ መውጣት አለባት፡፡
‹‹አሁንም እንደዚያ ይሆን ወይ?›› አልከኝ?
እንጃ በእውነቱ፡፡ ደረጃውን የጠበቀ መጸዳጃ ያለው ስንት ኢትዮጵያዊ ነው ብለህ ነው? የጤና ኤክስቴንሽኖች በ2000 ዓ.ም. ተማሪ ሳለሁ እየዞሩ ሽንት ቤት ሲያስቆፍሩ ተከትዬ እንዳያቸው ጋብዘውኝ ነበር፡፡ የሄድነው ሁሉም ነዋሪ ቆፍሬ እየተጠቀምኩ ነው ባለው መሰረት ክትትል በሚካሄድበት ቀን ስለነበረ አንዲት እማወራ ሊያሳዩን ወደ ጓሮ ወሰዱን፡፡
‹‹የታል?›› አለች ተቆጣጣሪዋ፡፡
‹‹የኸው››
‹‹የቱ?››
ሴትዮዋ ሽንት ቤት የሚሉት ሜዳውን ኖሯል፡፡
‹‹መች ቆፈራችሁ?›› ሲባሉ
‹‹አሁንማ ገብስ ተዘራበት›› ብለው እርፍ፡፡
አይ ከተምኛ ገበያ ሄዶ የሚገዛው ገብስ ምን ላይ እንደበቀለ አያውቅ!
ከዚያ ያቺ እትዬ ማንያዛታል (ስሟን እንደዚህ ያልኩት የወንድም የሴትም ቅልቅል ነገር ነች ስላልኩ ነው፡፡ የሁሉን አመል የያዘች፡፡ ያውም ያምስት፡፡)
ምናለፋችሁ ይቺ ማንያዛታል ማታ ዉኃ አልቀዳች ኖሮ አህያዋን ሁለት ሃያ ሊትር የሚይዙ ጀሪካኖችን ጭና ሌሊት ወደ አይጥ ዉኃ መገስገስ፡፡ ዉኃውን ጭና ስትመጣ ወፍ ጭጭጭጭጭ አለ፡፡ መቼም አርፍዶ የተነሳው ጎረቤት ቅናት ላይጣል፡፡ ‹‹ማልደሻል በይ›› አላት ጎረቤቷ አቶ አስደንግጥ፡፡ አልጎምጉማ ሰላምታ ሰጥታው አለፈች፡፡ ሁልጊዜ በልቧ ሰድባው ነው የምታልፈው፡፡ እሱና ሚስቱ በሐብት ስለሚበልጧት አትወዳቸውም፡፡ እንጨት አያይዛ፣ ወጥ አፍልታ (ሰርታ አይባልም እዚያ)፣ ለከብቶች ድርቆሽ ሰጥታ፣ በርካታ የረሳኋቸውን ተግባራት ፈጽማ ስትጨራርስ ፀሐይ ወጣች፡፡ ልጆቿና ባለቤቷ ገና መነሳታቸው ነው፡፡ ሜዳ ከመድረስ በዘለለ ምንም አልሰሩም፡፡ ቁርስ በላልተው ወደየሚውሉበት አቀኑ፡፡ ፈረቃው የሆነው ወደ ትምህርት ቤት፣ ወደ ሥራም የሚሄደው ወደ ሥራው ተሰማራ፡፡
መቼም ዓይናችንን ከሷ ላይ አንነቅልም፡፡ የምንከታተለው እሷኑ አይደል? ሰጎን ከእንቁላሏ ላይ ዓይኗን እንደማትነቅለው እኛም ከማንያዛታል ላይ አንነቅልም፡፡
ሁሉንም ወደየሚውልበት ከላከች በኋላ ስጥ እያሰጣች ሳለች ጡሩምባ ነፊ ሲነፋ ሰምታ ጆሮዋን ሰጠች፡፡ ‹‹የእትዬ አመዘን እህት ሞታለችና ለቅሶ ድረሱ ተባላችኋል!›› ሲል ለፈፈ፡፡ ከሩቅ የለፈፈው ሲቀርብ በደንብ ተሰማት፡፡ እድርተኛ ስለሆነች እየተራገመች ወደ ለቅሶ ቤቱ ሄደች፡፡ ዛሬም በድንገተኛ ነገር ያሰበችውን ሥራ ሳትከውን ልትውል ነው፡፡ ከለቅሶ ለመቅረትም አትፈልግም፤ አንድም እድሩ ይቀጣታል፤ አለያም ለሷ መከራ የሚመጣላት አይኖርም፡፡ ከዚህ ሰሞንማ ለቅሶ ብዝት ብሏል፡፡ በዚያ ላይ በዓሉ፤ በዚያ ላይ የሥራው ጫና፡፡ ታህሳስ የሰብል መሰብሰቢያ ወቅት ስለሆነ ስራ ይደራረባል፡፡ የቤቱ ብቻ ሳይሆን የዱሩም አይቀርላትም፡፡ በዚህ ወር ልጆቿን ሥራ እንዲያግዟት አንድ ሦስት ቀን ከትምህርት ቤት ማስቀረት ሳይኖርባት አይቀርም፡፡ ሰዉ ቀስ በቀስ ተሰበሰበ፡፡ ወዲያውኑ ቀብር ዕለቱን ስለሆነ ተከትላ አምባዋሻ ወረደች! ምን የመንገዱን ውጣ ውረድ፣ የዕለቱን ትዕይንት ምን እነግርሃለሁ! ስትመለስ 10 ሰዓት ሆኖ ነበር፡፡ ደክሟትም አረፍ ማለት የለም፡፡ ሴት ልጅ የለቻትም፡፡ ሦስቱም ወንዶች ናቸው፡፡ ምሳቸውን ራሳቸው በልተው ኖሯል፡፡ ወንድ ወጥ ስለማይሰራ እንጀራ በበርበሬ ነበር የበሉት፡፡ ፀሐይ ስትጠላልቅ ሜዳ ወጥተው መጡ፡፡ ከብት አበሉ፡፡ የከብቶቹን በረት ቆላለፉ፡፡ እናታቸው ምሽት ራት ሰርታ አበላቻቸው፡፡ እንቅልፍ እስኪወስዳት አላረፈችም፡፡ ሥራውም አያልቅላት፡፡ ሌሎቹ እሳት እየሞቁ ከማውራት፣ የቤት ሥራ ያላቸውም ከመሥራት የዘለለ የቤት ውስጥ ሥራ አላገዙም፡፡ ዛሬ ያለፋትን እህል ማስፈጨትና ለደቦ ድግስ መደገስ ነገ ትሠራለች፡፡ ለአሂዶ ከብቶች መለመኑንና ሌላውን የዱር ስራ ባሏ ይወጣል፡፡
በዚህች ትንሽ ከተማ ገበሬዎች ተሰባስበው ስለሚኖሩባት ከተማ አልናት እንጂ መሬት የሌለው እንደሌለ ባለፈው ተነጋግረናል፡፡ የሳሲቶችን የታህሳስ 1985 ዓ.ም. ሕይወት ሰላሳ ዓመት ወደፊት ተጉዞ ከዛሬ ጋር ማወዳደር የሚፈልግ ቢኖር ይበረታታል፡፡ ዉሱን ለውጦች ናቸው ያሉት፡፡ ዉኃ ቦኖ፣ መብራት በየቤቱ (የጎዳና የለውም)፣ ቴሌቪዥን፣ በየቀኑ ምድብ መኪና፣ ሞባይል፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ ከመኖሩ በቀር ብዙም ለውጥ የለም ለማለት ይቻላል፡፡ እትዬ ማንያዝሻል ዛሬ እርጅና ተጫጭኗት ዘመኑ ያመጣውን የመብራትና ዉኃ ትሩፋት ትጠቀማለች፡፡ የዕለት ውሎዋም እምብዛም አልተቀየረም፡፡ ያኔ ሱቅ ስር፣ ጠላ ቤት፣ መንገድ ዳር፣ አንዲት ጥጋት ሆኖ የሚያወራው ሰው አሁንም አለ፡፡ እትዬ በእርግጥ መሬቷን የእኩል ስለሰጠች የማሳ ላይ ሥራ ቀርቶላታል፡፡ ከብቶቹ ስላሉ ግን ሙሉ በሙሉ ከግብርና ርቃለች ለማለት አንችልም፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም:
አስተያየት ይለጥፉ